ቀጥታ፡

በቀጠናው የኢትዮጵያን ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥልጠና ማካሄዱን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ

ሐምሌ 26 ቀን 2014(ኢዜአ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ያካሄደው ሥልጠናዊ ግምገማ ተለዋዋጭ የደኅንነት ስጋት በተደቀነበት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የኢትዮጵያን ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል ግብዓት እንደተገኘበት አስታወቀ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለአራት ቀናት ያካሄደውን ሥልጠናዊ ግምገማ አጠናቋል፡፡

አገልግሎቱ መድረኩን አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የተቋሙ መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች ከተሳተፉበት አመታዊ የአፈጻጸም ግምገማ ጎን ለጎን በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ፣ ቀጣናዊ፣ ሀገራዊና ተቋማዊ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

በላቀ ተቋማዊና የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ዙሪያ፣ በሥነ ልቦና ጦርነት ንድፈ ሐሳብና ተሞክሮዎች፣ በተሻሻለው ዐዋጅ አተገባበር፣ በዓለም አቀፋዊ፣ ቀጣናዊና ሀገራዊ የደኅንነት ስጋቶችና መልካም አጋጣሚዎች እንዲሁም በሌሎችም ወቅታዊ የመረጃና ደኅንነታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠናው ትኩረት ማድረጉ ተመልክቷል።

በስልጠናዊ ግምገማው ተለዋዋጭ የደኅንነት ስጋት በተደቀነበት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የኢትዮጵያን ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ግብዓቶች እንደተገኘበት መግለጫው አስታውቋ፡፡

ተቋሙ በተያዘው በጀት ዓመት ያቀዳቸውን የመረጃና የደኅንነት ተልዕኮዎች በላቀ ደረጃ ለመፈጸም እገዛ እንደሚያደርግም አመልክቷል፡፡

በፍጥነት ተለዋዋጭ የሆነውን ዓለም አቀፋዊ፣ አካባቢያዊና ሀገራዊ ሁኔታዎች በተመለከተ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በመተንተንና ለአስፈጻሚ አካላት በማቅረብ መካሄዱ በመግለጫው ተጠቁማል።

ቴክኖሎጂዎችን ለተለያዩ ስምሪቶች በማዋል የደኅንነት ስጋቶችን በከፍተኛ ደረጃ ለማስቀረትም ዝግጅት መደረጉ የተረጋገጠበትና ቀጣይ አቅጣጫ የተቀመጠበት ሥልጠናዊ ግምገማ እንደነበርም ተገልጿል።

መድረኩ ሲጠናቀቅ በብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ችግኞች በመትከል አረንጓዴ አሻራ የማኖር መርሐግብር ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም