ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ እያሳየች ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ እያሳየች ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑ ተገለጸ
ሐምሌ 25 ቀን 2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ እያሳየች ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የህዝብ፣ የስደተኞችና የፍልሰት ጉዳዮች ምክትል ኃላፊዋ ኤልሳቤት ካምቤል ገለጹ።
ኃላፊዋ ከጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ ጋር በክልሉ በሚገኙ የስደተኞች አያያዝ ዙሪያ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በጋምቤላ ከተማ ተወያይተዋል።
ምክትል ኃላፊዋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ብሎም የጋምቤላ ክልል መንግስት ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ ረገድ ያለውን ቁርጠኝነት የአሜሪካ መንግስት በእጅጉ የሚያደንቀው ተግባር ነው።
ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ እያደረገች ላለው ድጋፍና ጥበቃ የአሜሪካ መንግስት የሚያደርገውን የፋይናንስ ድጋፍ አጠናከሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
የባይደን አስተዳደር ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ሰብአዊ አገልግሎት የሚውል 135 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው በቀጣይ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ የኢትዮጵያ ብሎም የክልሉ መንግስት ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ በኩል የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት በርካታ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን በመቀበል መጠለያ ብቻ ሳይሆን ያለውን ውስን ሀብት በማጋራት ጭምር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ለስደተኞች የሚደረገው ጥበቃና ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ።
ኃላፊዋ በነገው እለት በክልሉ የሚገኙ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን ተዘዋውረው እንደሚጎበኙ በውይይት መድረኩ ላይ ተገልጿል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ