ቀጥታ፡

ለአረንጓዴ አሻራ ልማት ስኬታማነት የመገናኛ ብዙሃን የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

ደብረ ብርሃን፤ ሐምሌ 25/2014(ኢዜአ) ፡- እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላና ልማት እንዲሳካ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በኩል የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

በደን ልማት ሀብት አጠቃቀምና አዘጋገብ ዙሪያ ከጋዜጠኞች ጋር በደብረ ብርሃን ከተማ ምክክር ተካሄዷል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም በወቅቱ  እንዳሉት፤ የሀገሪቱን የደን ሽፋን በማሻሻል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በትኩረት እየሰራ ነው።

በቀደሙት ሶሰት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ18 ቢሊየን በላይ ችግኝ መትከል እንደተቻለ ጠቅሰው፤ በተያዘው የክረምት ወቅትም እስካሁን 5 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኝ መተከሉን ገልጸዋል።

ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ   አህመድ በአራት ዓመታት  20 ቢሊዮን  ለመትከል ይፋ ያደረጉትን ዕቅድ   ማሳካት እንደተቻለ ነው ያመለከቱት።

በሀገሪቱ እያደገ የመጣው የኢንቨስትመንት ፍሰት፣ የማገዶ ፍላጎት፣ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋትና የበረሃማነት መጨመር  ጋር ተያይዞ የሚያስትለውን ችግር ለመከላከል  የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ፍቱን መፍትሄ ነው ብለዋል።

የመገናኛ ብዙሃን  ባለሙያዎች ባለፉት ጊዜያት ባከናወኑት ስራ   ህብረተሰቡ ስለ ደን ሃብት ጠቀሜታና ችግኝ ተከላ ያለው ግንዛቤ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ሆኖም ከችግሩ ስፋት አንፃር አሁንም ዘላቂ በማድረግ በኩል ስራዎች ይጠይቃሉ ብለዋል።

ህብረተሰቡ የጀመረውን ችግኝ ተከላ እንዲያጠናክር ፣ የተተከሉትን በመንከባከብ፣ የተፈጥሮ ደኖችን በመጠበቅና በማልማት ስራው  እንዲቀጥል ግንዛቤውን በማሳደግ በኩል  የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች  እንደ ወትሮ ሁሉ ወደፊትም  የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የደብረ ብርሃን እንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ባዩ ደጀኔ ፤ ፋብሪካው ለግንባታ  ግብዓት የሚውል ተነባባሪ ጣውላ በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ  መሆኑን ገልጸዋል።

የደን ልማቱን ስራ ከፋብሪካው ማምረት ጋር በማስተሳሰር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸው፤ ፋብሪካው ከውጭ የሚገባን ጣውላ ተክቶ ለገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዓመት 40 ሺህ ሜትሪክ ኩብ እንጨት በመጠቀም 200 ሺህ ጣውላ በማምረት 170 ሚሊየን ብር በላይ ግብይት ያካሂዳል ብለዋል ስራ አስኪያጁ።

የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩም የሃገሪቱን የደን ሃብት ከማሻሻሉም በላይ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት በስፋት እንዲያገኙ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የአሚኮ ጋዜጠኛ ማርታ ጌታቸው በበኩሏ፤ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ጥልቀት ያለው መረጃ በመስጠት ዘላቂነቱን ማረጋገጥ ይገባል ብላለች።

በተለይም የደን ሃብት ልማቱ የአየር ንብረት ልውጥ ከመቋቋም ባሻገር ለሃገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ያለውን ጠቀሜታ በማሳየት ህብረተሰቡ በስራው ተሳትፎን እንዲቀጥል ለማነሳሳት በሙያዋ የበኩሏን አስተዋጽኦ እንደምታደርግ ተናግራለች።

ከትናንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት  በተካሄደው የምክክር መድረክ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተወጣጡ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም