ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና አንጎላ በኢኮኖሚ ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከስምምነት ላይ ደረሱ

ሐምሌ 25 ቀን 2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያና አንጎላ በኢኮኖሚ ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገለፁ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ከሚገኙት የአንጎላ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴቴ አንቶኒዮ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ ከአንጎላ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሰራ የገለፁ ሲሆን በተለይም በኢኮኖሚ ዘርፍ በተለያዩ መስኮች ላይ ተባብሮ መስራት እና አማራጮችን ማስፋት እንደሚገባ ገልፀዋል።

መንግሥት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ የወሰዳቸውን እርምጃዎችን አቶ ደመቀ አብራርተዋል።

የተኩስ አቁም ስምምነት፣ያልተገደብ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት፣ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ገለፃ አድርገዋል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል።

መንግሥት በአፍሪካ ህብረት መሪነት ለሚካሔደው የሰላም ድርድር ቁርጠኛ በመሆን ተደራዳሪ ቡድን ሰይሞ ወደ ሥራ መግባቱን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ በማንኛውም ጊዜ የሰላም ድርድሩን ለመጀመር ዝግጁ ነው ብለዋል።

ከህወሓት ቡድን በኩል ግን የአፍሪካ ህብረትን ጥረት የማጣጣል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

የአንጎላው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴቴ አንቶኒዮ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ሀገሪቱ ያጋጠማትን ችግር ለማለፍ እየወሰዳቸው ያሉትን እርምጃዎች አድንቀዋል ።

"ኢትዮጵያ በነጻነት ትግላችን ወቅት ባለውለታችን ነች" ያሉት ሚኒስትሩ ያን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ኢኮኖሚ ግንኙነት መለወጥ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በአህጉር አቀፍ ደረጃ ለሚፈፀሙ የኢኮኖሚ ስትራቴጂዎች ተፈጻሚነትም በጋራ መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያና አንጎላ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1979 መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም