ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሳዑዲ አረቢያ ገቡ

ጂዳ መስከረም 5/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነትን በሚመለከት ሳዑዲ አረቢያ ባዘጋጀችው የእውቅና ዝግጅት ላይ ለመታደም ዛሬ ማምሻውን ጂዳ ገቡ። በዚህ ዝግጅት ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተጨማሪ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በስፍራው ተገኝተዋል። ኢትዮጵያና ኤርትራ ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ የቆየውን የጥላቻ ፖለቲካ ትተው ሰላማዊ ግንኙነት ከመሰረቱ ወራት ተቆጥረዋል። የአገራቱ መሪዎችንና የጦር ሰራዊት አባላትን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት የዘንድሮው የኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ በዓል ሰሞኑን በትግራይ ክልል ዛላንበሳ ከተማ ተከብሯል። ይህም በሁለቱ አገራት መንግስታት መካከል የተጀመረው ሰላማዊ ግንኙነት ወደ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲያድግ አድርጎታል። ኢትዮጵያና ኤርትራ የምጣኔ ኃብታዊ ትብብራቸውንም ለመቀጠል የተስማሙ ሲሆን ከሳምንታት በፊት ኢትዮጵያ የአሰብንና ምፅዋ ወደቦችን መጠቀም ጀምራለች። በሁለቱ አገሮች መካከል በተፈጠረው ሠላም ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ  ሳዑዲ የአገሪቷን ከፍተኛ ኒሻን መሸለሟ ይታወቃል። በሳዑዲ ከሚካሄደው እውቅና በተጨማሪ በኢትዮጵያ አስተባባሪነት በኤርትራና ጅቡቲ የተጀመረው የሰላም ስምምነት የዝግጅቱ አንዱ አካል እንደሚሆን ይጠበቃል። በዝግጅቱ ላይ የሳዑዲው አልጋ ወራሽ እንዲሁም የጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም