በክልሉ በባህላዊ ወርቅ ምርት ስራ የተሰማሩ ማህበራት ከ94 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በባህላዊ ወርቅ ምርት ስራ የተሰማሩ ማህበራት ከ94 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ አቀረቡ
ሐምሌ 25 ቀን 2014(ኢዜአ) ባለፈዉ በጀት አመት በክልሉ በባህላዊ ወርቅ ምርት ስራ የተሰማሩ ማህበራት ከ94 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ማቅረባቸውን የአፋር ክልል ማእድን ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
እየተካሄደ በሚገኘዉ የአፋር ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ የክልሉ ማእድን ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገዶ ሀሞሎ ለምክር ቤቱ እንደገለጹት ለዉጡን ተከትሎ በክልሉ የማእድን ልማት ሴክተሩ ላይ የነበሩ የአሰራር ችግሮችን ለመፍታት በተሰሩ የሪፎርም ስራዎች አበረታች ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን አሰረድተዋል፡፡
ከዚህም ውስጥ የጨውና የወርቅ ማእድን ልማት ዘርፉ በዋናነት ይጠቀሳል ብለዋል፡፡
በተለይም ወርቅ በክልሉ በዋናነት በኪልበቲ-ረሱ ዞን ኩነባ፣ በራህሌ፣ ዳሉልና ኢረብቲ ወረዳዎች ከፍተኛ የወርቅ ሃብት እንደሚገኝ ጥናቶች እንደሚያሳዩ ገልጸዋል፡፡
ይሁንና እስካሁን በብዛት ወርቅ እየተመረተ የሚገኘዉ ከኩነባ ወረዳ ቢሆንም ምርቱ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በህገወጥ መንገድ በተለያዩ ግለሰቦች ሲመዘበር መቆየቱን አንስተዋል፡፡
ከሪፎርሙ በኋላ የክልሉ መንግስት ይህን ህገ-ወጥ አሰራር ወደ ህጋዊ መስመር ለማስገባት ከብሄራዊ ባንክ ጋር በመነጋገር ኩነባ ወረዳ ላይ ቅርንጫፍ እንዲከፍት ማድረግ ተችሏል ነው የተባለው፡፡
ይህ በፈጠረዉ መነቃቃትም በነዚህ አካባቢዎች ክልሉ ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በ12 ማህበራት ተደራጅተዉ በባህላዊ መንገድ ወርቅ እያመረቱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ከነዚህ አምራቾች ወርቅ እየገዙ ለብሄራዊ ባንክ በማቅረብ ስራ ላይ ተሠማርተዉ የሚገኙ ከ290 በላይ አባላት በ5 ማህበራት የተደራጁ ወርቅ አዘዋዋሪነት ስራ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በ2012 በጀት አመት ጀምሮ ክልሉ ለመጀመሪያ ግዜ ለብሄራዊ ባንክ ወርቅ ማቅረብ መጀመር መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
ባለፈዉ በጀት አመትም በክልሉም ሆነ እንደ ሀገር የገጠሙ ወቅታዊ የጸጥታ ችግሮችን ከግምት በማስገባት ክልሉ 50 ኪሎ-ግራም ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ለማቅረብ አቅዶ እንደነበር አቶ ገዶ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡
ይሁንና ህብረተሰቡ በህጋዊ መንገድ በተፈጠረለት የገበያ ትስስር የተሻለ ጥቅም በማግኘቱ አፈጻጸሙ ከእቅዱ በላይ 189 በመቶ እድገት በማሳየት ከ94 ኪሎግራም በላይ ወርቅ በማህበር የተደራጁ 5 ወርቅ አቅራቢዎች ለብሄራዊ ባንክ ማቅረባቸዉን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ወርቅ አቅራቢ ማህበራቱ ከ348 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻላቸዉን ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ምክር ቤት ባለፉት ሁለት ቀናት የክልሉን 2014 እቅድ አፈጻጸም፣ የጠቅላይ አቃቢ ህግና ዋና ኦዲተር የኦዲት ሪፓርት ዙሪያ እየተወያየ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ