ስድስተኛው አገር አቀፍ የውሃ፣የውሃ ዲፕሎማሲና ኢነርጂ ፎረም በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ስድስተኛው አገር አቀፍ የውሃ፣የውሃ ዲፕሎማሲና ኢነርጂ ፎረም በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ይካሄዳል
ሐምሌ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ)ስድስተኛው አገር አቀፍ የውሃ፣የውሃ ዲፕሎማሲና ኢነርጂ ፎረም በመጪው መስከረም ወር በባህር ዳር እንደሚካሄድ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
መስከረም 8 እና 9 ቀን 2015 ዓ.ም የሚካሄደው ፎረም በናይል ተፋሰስ አገራት በዝናብና ውሃ እጥረት የሚከሰት ድርቅ፣በውሃ ዲፕሎማሲ ኮምዩኒኬሽን ያለው ሚና፣የውሃ ዲፕሎማሲ ትግበራ አስመልክቶ ያሉ ተሞክሮዎች እና የናይል ተፋሰስ የውሃ ሀብቶችና የውሃ ፍሰትና ክምችት ሚዛን(በተለይም በታችኛው የናይል ተፋሰስ የከርሰምድር ውሃ ላይ ያተኮረ) ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸው ገልጿል።
ምሁራን እና ተመራማሪዎች በቀረቡት ርዕሶች ላይ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን አዘጋጅተው እስከ ነሐሴ 19 ቀን 2014 ዓ.ም ለሚኒስቴሩ እንዲያስረከቡ ጥሪ ቀርቧል።
አምስተኛው አገር አቀፍ የውሃ፣የውሃ ዲፕሎማሲና ኢነርጂ ፎረም በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ነው።
በፎረሙ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና መገናኛ ብዙሃንን ያካተተ የኢትዮጵያ የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረም መመስረቱ ይታወቃል።
መማክርት ፎረሙ በግድቦች እና ውሃ ሀብት አስተዳደር ጉዳዮች ሙያዊ ድጋፍ መስጠት፣ዘርፉን የሚያሳድጉ ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳቦችን ማቅረብና የሰራቸውን ውጤቶች በመገናኛ ብዙሃን የማሰራጨት ተግባር እንደሚያከናውን በምስረታው ወቅት መገለጹ ይታወቃል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ