ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የቡና ኤክስፖርት በ15 ዓመታት ውስጥ ወደ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ በስትራቴጂክ እቅድ ተይዟል

ሀምሌ 25/2014/ኢዜአ/የኢትዮጵያን የቡና ኤክስፖርት በ15 ዓመታት ውስጥ ወደ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ በስትራቴጂክ እቅድ መያዙ ተገለጸ።

ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ የንግድ ማዕከል በጄኔቫ ስዊዘርላንድ በተዘጋጀው የቡና ቅምሻ ፕሮግራም ላይ ተሳትፋለች።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዘነበ ከበደ በመርሃ ግብሩ ላይ በኢትዮጵያ ቡና ምርት ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች እና እንቅፋቶች፣ ብሎም የቡናን ዘርፍ ለማሳደግ የመንግስት አጠቃላይ ስትራቴጂ ምን እንደሚመስል ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡

በቅርቡ በወጣው ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂ መንግስት ችግሮቹን ለመፍታትና የኢትዮጵያን የቡና ምርት በ15 ዓመታት ውስጥ ወደ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ አንስተዋል፡፡

የአርሶ አደሩን ገቢ ወደ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ እና የስራ እድል ለመፍጠር ስትራቴጂ መነደፉን ጠቁመው በ2033 በአለም ገበያ የምታቀርበው የዓለም ገበያ ድርሻ በ2033 ወደ 1 ነጥብ 26 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ለማድረስ መታቀዱን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በሂደት ላይ ስትሆን፣ አምባሳደር ዘነበ የሀገሪቱን የመቀላቀል ሂደት በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ሁለንተናዊ የቴክኒክ እና የፕሮጀክት ተኮር ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ዓለም አቀፍ ንግድ ኮሚሽንን ጠይቀዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ ቡና ስነ-ስርዓት ለታዳሚዎች ቀርቧል።

የቡና ቅምሻ መርሃ ግብሩ የዓለም አቀፍ ንግድ ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ማርሴል ቬርኖኢጅ፣ የኔዘርላንድ ቋሚ ተወካይ የዓለም አቀፍ ንግድ ኮሚሽን ዋና የኢኮኖሚ እና ልማት ክፍል በጄኔቫ፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች እና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም