ቀጥታ፡

በጦርነቱ የሰነ-ልቦና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል- ሚኒስቴሩ

ሰመራ ሀምሌ 24/2014 (ኢዜአ ) በአፋር ክልል አሸባሪው ህወሐት በከፈተው ጦርነት የሰነ-ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች አገግመው ወደ መደበኛ ኑሯቸዉ እንዲመለሱ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አቀረበ።

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት በአፋር ክልል በጦርነቱ ምክንያት ተጎጂ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የተቀናጀ ተግባራዊ የሰነልቦና ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል የተዘጋጀ የባለድርሻ አካላት ስልጠና ዛሬ በሰመራ ከተማ መሰጠት ጀምሯል።

በስልጠናው ላይ  የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ጹጉማ እንደተናገሩት የሽብር ቡድኑ በሀገር ላይ ደቅኖ የነበረዉ የህልውና አደጋ በዜጎች ሁሉን አቀፍ ርብርብ ተቀልብሷል።

"በሂደቱ ሴቶችና ህጻናት ተደፍረዋል ፤እንዲሁም በየአካባቢው በተፈጸሙ አሰቃቂ ጭፍጨፍና ተያያዥ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዜጎች ለከፋ-ስነ-ልቦናዊ ቀውስ ተጋልጠዋል"  ብለዋል።

ተጎጂ  የህብረተሰብ ክፍሎች ጦርነቱ ካደረሰባቸው አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ቀውስ አገግመዉ መደበኛ ህይወታቸውን በአግባቡ መምራት አንዲችሉ ባለድርሻ አካላት  ከየትኛውም ጉዳይ በላይ ትኩረት ሰጥተው በቅንጅት ድጋፍ ሊያደርጉና ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

መንግስት ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት እንዲሁም ከሃይማኖት አባቶችና ተያያዥ የማህበረሰብ መሪዎች ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ስልጠናው የዚሁ አንድ አካል መሆኑን ጠቁመው  የጤና፣ የሰነ-ልቦናና፣ተያያዥ ባለሙያዎች በቀጣይ ከስልጠናው የሚያገኙትን  እውቀት ተጠቅመው ወደ ህብረተሰቡ ወርደው የዜጎችን ሰነልቦናዊ ችግር ለመቅረፍ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ እታገኘሁ አሰፋ በበኩላቸው "ጦርነቱ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ካስከተለው አሉታዊ ተጽእኖ በተጨማሪ በዜጎች ላይ ውስብስብ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ጉዳት አስከትሏል" ብለዋል።

በተለይም በአፋርና አማራ ክልሎች ሽብር ቡድኑ በየደረሰበት ሴቶችና ህጻናትን ተደፍረዋል፤ በሌሎች ወገኖች ላይም ተገልጾ የማይልቅ የስነ-ልቦና ተያያዥ ጉዳቶችን አስከትሏል " ሲሉም ጠቁመዋል ።

 ዜጎች ከደረሰባቸዉ ጉዳት ፈጥነው አገግመው ወደቀደመ ህይወታቸው እንዲመለሱ የሁሉንም ድጋፍ እንደሚፈልጉ አመልክተዋል።

ከዚህ አኳያ የሴቶቸና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴርና የጤና ሚኒስቴር ከክልልና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የሰነ-አእምሮና ስነ-ልቦና ጤና እንዲሁም ተያያዥ ማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የጋራ እቅድ አውጥተው ወደ ተግበራ መሸጋገራቸውን አስታውቀዋል።

ይህን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ በአፋር ከልል ከ3ዞን የተዉጣጡና ወደማህበረሰቡ ወርደዉ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል

የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ በበኩላቸዉ ጦርነቱን ተከትሎ በህብረተሰቡ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና አደጋዎችን በፍጥነትና በጥራት ለመቆጣጠር አንዲቻል ኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ ማህበረሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማእከል በማዋቀር የተለያዩ ስራዎችን ሲሳራ መቆየቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአማራና አፋር ክልሎች  ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የስነ-አእምሮና ስነ-ልቦና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት በዘርፉ የሚስተዋሉ የባለሙያዎች እጥረትን ለመቅረፍ ስልጠና በመስጠት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል ።

የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ኑሩ መሀመድ በኩላቸው "ከዚህ በፊት ለሰብአዊ ድጋፍና መልሶ ግንባታ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ በዜጎች ላይ ያንዣበበን አደጋ መቀነስ ተችሏል" ብለዋል።

"ይሁንና እንደሀገር በነበሩ ተደራራቢ ችግሮች ምክንያት በዜጎች ላይ የደረሰውን ሰነልቦና ቀውስ ለማቃለል የተሰሩ ስራዎች ውስንነት ነበረባቸው "  ብለዋል።

ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የተቀናጀ የሰነልቦና ድጋፍ ለመስጠት እየተደረጉ የሚገኙ ጥረቶች ዜጎች ከደሰረሰባቸው ጉዳት አገግመው ጤናማና አምራች እንዲሆኑ በማድረግ የማይተካ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመላክተዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀን በሚሰጠው ስልጠና ላይ ከሶስት ዞኖች የተውጣጡ ከ300 በላይ የጤናና ሰነልቦና ባለሙያዎች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም