ቀጥታ፡

የባህር ዳር ከተማ ፀጥታ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስተማማኝ ሆኗል

ባህር ዳር (ኢዜአ)፣ሃምሌ 24/2014 የባህር ዳር ከተማ ፀጥታ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስተማማኝ ሆኗል የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ገለጹ።

በከተማው በፀጥታ ማስከበር ስራ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፖሊስ አባላት ዛሬ የእውቅናና ምስጋና ስነስርአት ተካሂዷል።

የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ እንዳሉት የከተማው ፖሊስ አባላት በህልውና ዘመቻው የህይወት መስዋትነት ጭምር በመክፈል አኩሪ ድል ጽፈዋል።

"በከተማ አስተዳደሩ ተንሰራፍቶ የነበረውን ህገ ወጥ ድርጊቶች ለማስቆም በተካሄደ የህግ ማስከበር ዘመቻ የፀጥታ አባላቱ ህገ ወጦችን ፊት ለፊት ተጋፍጠው ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ ችለዋል" ነው ያሉት።

በተሰራ ስራም አሁን ላይ ባህርዳር ከተማ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሰላም አየር የሚተነፍስባት ከተማ ማድረግ ተችሏን ብለዋል።

የህግ ማስከበር ስራውም የህዝቡን ተደጋጋሚ ጥያቄ የመለሰ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለተገኘው ውጤት የጸጥታው ሃይል ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በቁርጠኝነት ወንጀለኞችን ለይቶ በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረጉ እንደሆነም አመልክተዋል።

''ከተማዋን ለነዋሪውና ለቱርስቶች የበለጠ ምቹ ከማድረግ ባለፈ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የተጀመሩ ሰላምን ዘላቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል'' ብለዋል።

ዛሬ የተሰጠው የእውቅናና የሜዳሊያ ሽልማቱ የፖሊስ አባላቱ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ተገቢውን እውቅና ለመስጠትና በቀጣይ ጠንካራ ስራዎችን ለመስራት የሚያበረታታ መሆኑን የከተማው ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር አትንኩት አያሌው አስረድተዋል።

የፖሊስ አባላቱ ወንጀሎኞችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ ተጠያቂ  እንዲሆኑ በማድረግ በኩል የሚያስመሰግን ስራ ማከናወናቸውን ገልፀዋል።

"አሁን ላይ በከተማው ህገ-ወጦች እንደፈለጋቸው ጥይት በመተኮስ የህዝቡን ሰላም ማወክ ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ማድረስ ተችሏል" ብለዋል።

በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ግድፈቶችን ለማስተካከልም በቀጣይ ይሰራል ነው ያሉት።

''የባህር ዳር ከተማን ሰላም አስተማማኝ በማድረግ ተመራጭ የቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን የተጀመሩ ስራዎች ህዝቡን በማሳተፍ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባል'' ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ ናቸው።

ህብረተሰቡ ህግን ለማስከበር በሚከናወኑ ተግብራት በተመለከተ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማህበራዊ ሚዲያ የሚያራግቡ ግለሰቦችን ባለመቀበል ለእውነተኛ ሰላም መከበር ከሚታገሉት የጸጥታ አካል ጎን መቆም እንደሚገባው አሳስበዋል።

ህብረተሰቡ ለፖሊስ ወሳኝ አጋር በመሆን የባህርዳርን ሰላም አስተማማኝ በማድረግ የቱሪዝም መዳረሻነቷን የበለጠ ለማጠናከር እንዲተጋ መልእክት አስተላልፈዋል።

በተሰጣቸው እውቅና መደሰታቸውንና ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳቸው መሆኑን የገለጹት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ምክትል ኢንስፔክተር መሠረት ደመቀ ናቸው።

በስነ-ስረዓቱ ላይ የክልል የፀጥታው ዘርፍ አመራሮችና የከተማው ነዋሪዎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም