ምዕምኑ ለፈጣሪው ምስጋና ሲያቀርብ ይቅር በመባባልና በትብብር ወደ ተሻለ ነገ ለመሻገር በመሥራት ሊሆን እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
ምዕምኑ ለፈጣሪው ምስጋና ሲያቀርብ ይቅር በመባባልና በትብብር ወደ ተሻለ ነገ ለመሻገር በመሥራት ሊሆን እንደሚገባ ተጠቆመ
ሀምሌ 24/2014(ኢዜአ) ምዕምኑ ለፈጣሪው ምስጋና ሲያቀርብ ይቅር በመባባልና በትብብር ወደ ተሻለ ነገ ለመሻገር በመሥራት ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን አባቶች ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን በዛሬው እለት "ኢትዮጵያ ታመስግን" መርሃ-ግብር አከናውነዋል።
ኢዜአ መርሃ-ግብሩ በተካሄደበት ጦር ኃይሎች አካባቢ በሚገኘው በቀጣና ሁለት አጥቢያ ቤተክርስቲያን ያነጋገራቸው የቤተክርስቲያኗ አባቶች የሰው ልጅ ለተደረገለት መልካም ነገር ፈጣሪውን ሊያመሰግን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የቤተክርስቲያኗ የመሪዎች ሰብሳቢ ፓስተር ደሴ ተሰማ ምስጋና ከፈጣሪ ጋር ሕብረት የሚደረግበትና በትብብርና በመተጋገዝ ለመኖር የሚያግዝ በጎ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ ደግሞ ለአገር አንድነትና ሰላም የራሱ የሆነ በጎ ሚና አለው ነው ያሉት።
በመሆኑም ምዕመኑ በምስጋና ወቅት በአንድ ልብ ሆኖ ይቅር በመባባል ፈጣሪውን ማመስገን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ምስጋና የመንፈስ አንድነትን ጠብቆ ወደ ነገ በክብር ለመሻገር የሚረዳ መሆኑንም እንዲሁ፡፡
የቤተክርስቲያኗ መጋቢ ተመስገን ብርሃኑ በበኩላቸው፤ ''ምስጋናን የሚሰዋ እሱ ያከብረኛል'' በሚለው መሰረት በሕብረት ሆኖ ፈጣሪን ማመስገን ለቀጣይ ዓመት ብሩህነት ወሳኝ ነው ብለዋል።
''በፈተና ብቻ ሳይሆን ፈጣሪን በማንኛውም ሁኔታ ማመስገን ሊለመድና ባህል ልናደርገው የሚገባ ተግባር ነው'' ብለዋል፡፡
ሁሉም ሰው አንድ የሚሆነው ትኩረቱን ወደ ፈጣሪ ሲያደርግ በመሆኑ ሰዎች ለምስጋና ዝግጁ መሆን እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
ምስጋና ቀጣዩን ዓመት በመልካም ለመጀመርና የተሻለ ነገን ለመፍጠር ያግዛል ያሉት ደግሞ የቤተክርስቲያኗ ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር ኃይሌ ጉታ ናቸው።
መርሃ-ግብሩ እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በመላው አገሪቱ የጸሎትና ምስጋና መርሃ-ግብር እንዲካሄድ ጥሪ ማድረጉን ተከትሎ ነው፡፡