የኢንደስትሪና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች በአረንጓዴ አሻራ ልማት ግንባር ቀደም ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢንደስትሪና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች በአረንጓዴ አሻራ ልማት ግንባር ቀደም ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል
ጅማ፣ ሀምሌ 24/2014(ኢዜአ) የኢንደስትሪና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ለካርበን ልቀቱ ባለቸው አስተዋጽዎ ልክ በአረንጓዴ አሻራ ልማት ግንባር ቀደም ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተመለከተ ።
ዛሬ በደቡብ ክልል የም ልዩ ወረዳ "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ቃል የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላና የአቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎችን መኖሩያ ቤቶች የማደስ መርሀ ግብር ተከናወነ።
በመርሀግብሩ የተገኙት የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ እንዳሉት የኢንደስትሪና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ለካርበን ልቀቱ ባላቸው አስተዋጽዎ ልክ በአረንጓዴ አሻራ ልማት ግንባር ቀደም ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
"የመንግስት የልማት ድርጅቶች የአካባቢ አየር ብክለትን ለመከላከል በሚሰራው ስራ ሀላፊነት በመውሰድ አካባቢን በማልማት ማካካስ ይገባቸዋል "ብለዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ አክለውም የአረንጎዴ አሻራ ልማት ፕሮጀክት በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቅንበት እና በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኞች ተተክለው የጸደቁበት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
የአካባቢ የአየር ሚዛን የመጠበቅ ጉዳይ ትልቅ አለም አቀፍ አጀንዳ መሆኑን የገለጹት ስራ አስፈጻሚው የተሻለች ሀገር ለትውልድ የማስተላለፍ ትልቅ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል የዘርፍ አስተባባሪ አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው "ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሀገራችንን የተሻለች ለማድረግ የበለጠ በስራት ያስፈልገናል" ብለዋል።
"ሀገሪቱ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያስተባብር በመሆኑ ለጋራ ተጠቃሚነታችን አካባቢያችንን ውብ ማድረግ ያስፈልጋል" ሲሉም ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም የመንግስት የልማት ተቋማት ለአካባቢ ውበትና ልምላሜ ሰራተኞቻቸውን በማሳተፍ ላደረጉት አበርክትዎ ምስጋና አቅርበዋል።
"በልዩ ወረዳው ለሚደረግ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታና ለትምህርት ቁሳቁስ መግዢያ ተቋማቸው 200 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት ደግሞ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ገብረማርያም ናቸው።
የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ለአረንጓዴ አሻራው መርሀግብርና ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሀግብር ሰራተኞቹን በማሳተፍ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
የየም ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ገብረሚካዔል በበኩላቸው "በልዩ ወረዳው በ38ቱም ቀበሌዎች 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን የዛፍ ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል" ብለዋል።
ከ24ሺ በላይ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን በማስተባበር በሁሉም ቀበሌዎች 110 ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የበጎ ፍቃድ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
ልዩ ወረዳው በርካታ የግብርና ትራክተሮችና ማሺነሪዎች የሚያስፈልጉት መሆኑን በመግለጽ የመንግስት የልማት ጅርጅቶች ለወረዳዋ የግብርና ልማት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም የህብረተሰቡን የስራ እድልና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የኢንደስትሪ ፖርኮችና የግብርና ምርቶችን የሚጠቀም ፋብሪካ ቢገነባልን" ሲሉም ጠይቀዋል ።
የመንግስት የልማት ድርጅቶች የሆኑ 12 ተቋማት እያንዳንዳቸው 200 ሺህ ብር በማዋጣት በልዩ ወረዳው ለአቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች የመኖሪያ ቤት ና ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ግዥ የሚውል 2 ነጥብ 4ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸው ተመላክቷል።