ቀጥታ፡

ለተደረገልን ሁሉ ፈጣሪን በማመስገን መለያየትና ጥላቻ ተወግዶ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን መሥራት ይገባል

ሐምሌ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ)ለተደረገልን ሁሉ ፈጣሪን በማመስገን መለያየትና ጥላቻ ተወግዶ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን መሥራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጥሪ አቀረበች፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን "ኢትዮጵያ ታመስግን" መርሃ-ግብርን ዛሬ በ5 ኪሎ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን አካሂዳለች።

በመርሃ-ግብሩ ላይ በቤተክርስቲያኗ ሥርዓት መሰረት ፈጣሪ ላደረገው ሁሉ ምስጋና በማቅረብ ለአገር ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ለታመሙት ፈውስ እንዲሆን ጸሎት ተደርጓል።

በኢትዮጵያ መለያየትንና ጥላቻን አርቆ አንድነትንና ሰላም እንዲሰፍንም ጸሎት ተደርጓል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ-ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ አብርሃም ፈጣሪን ማመስገን የቤተክርስቲያኗ የዘወትር ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ቤተክርስቲያኗ በዛሬው እለት ደግሞ በሃይማኖት አባቶች አማካኝነት የቀረበውን ጥሪ ተቀብላ "በተለየ መልኩ" የምስጋና መርሃ-ግብር ማከናወኗን ተናግረዋል፡፡

ለተደረገልን ሁሉ ፈጣሪን በማመስገን መለያየትና ጥላቻ ተወግዶ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን መጸለይ እንደሚገባም ነው መልዕክት ያስተላለፉት፡፡

የተቸገሩትን በመርዳትና እርስ በርስ በመተጋገዝ ትውልዱ አመስጋኝ እንዲሆን መሥራት እንደሚገባም ብጹዕ አቡነ አብርሃም ተናግረዋል።

የእምነቱ ተከታዮች በበኩላቸው ምስጋናን ለተደረገልን ሁሉ ማቅረብ ይገባል ብለዋል፡፡የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ"ኢትዮጵያ ታመስግን" በሚል በመላው አገሪቱ የምስጋና ጸሎት መርሃ- ግብር እንዲደረግ ያስተላለፈውን ጥሪ ተከትሎ ቤተ-እምነቶች ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን መሰረት በማድረግ መርሃ-ግብሩን ማካሄዳቻው ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም