ዲያስፖራው በዲጅታል ዲፕሎማሲ ያሳየው የሀገር ደጀንነት የጎላ ነው- አምባሳደር ብርቱካን አያኖ - ኢዜአ አማርኛ
ዲያስፖራው በዲጅታል ዲፕሎማሲ ያሳየው የሀገር ደጀንነት የጎላ ነው- አምባሳደር ብርቱካን አያኖ
ጅማ፤ ሐምሌ 23/2014 (ኢዜአ)፡ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ሀገር በተፈተነችበት ወቅት በዲጅታል ዲፕሎማሲ ያሳየው የሀገር ደጀንነት የጎላ እንደ ነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተናገሩ።
በታላቁ ጉዞ ከዒድ እስከ ዒድ መርሐግብር ወደ ሀገር ቤት የመጡ የዲያስፖራ አባላትን ያሳተፈ ሲምፖዚየም ዛሬ በጅማ ከተማ ተካሂዷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ሀገር በውጭ ሀገራት ጫና በተፈተነችበት ወቅት ዲያስፖራው የሀገሩን አቋም ለመላው ዓለም በማሳወቅ የፈጸመው አኩሪ ተግባር ታሪክ አይረሳውም።
በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በዲጂታል ዲፕሎማሲ ለሀገራቸው ያበረከቱት አስተዋጽዎ ውጤታማ መሆኑን ጠቁመው፤ ''ለዚህም ምስጋናና ክብር ይገባቸዋል'' ብለዋል።
የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ነጂብ አባራያ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለእስልምና እምነት ማደግና መስፋፋት ያበረከተችው አስተዋፅኦ ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።
ጅማና ንጉስ አባጅፋር በኢትዮጵያ እስልምና ታሪክ ውስጥ የነበራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በሀገር ግንባታና በዲፕሎማሲው ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እንደነበረው ጠቁመዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት በታላቁ ጉዞ ከዒድ እስከ ዒድ መርሐ ግብር ወደ ሀገር ቤት መጥተው የሀገርን ትክክለኛ ገፅታ በመመልከት የልማቱ ተሳታፊ መሆን መጀመራቸውን የተናገሩት ደግሞ
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እድሪስ ናቸው።
''በውጩ ዓለም ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለውን የተዛባ እሳቤ በማስተካከል ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በጋራ እንስራ'' በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ ኡስታዝ አቡበከር አህመድና ሌሎች የፌዴራልና የክልል አመራሮች ተገኝተዋል።