በፈተና ውስጥ ድል ያጎናፀፈን ፈጣሪን እያመሰገንን በፅናት መቆም ይገባናል - የቤተክርስቲያን አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
በፈተና ውስጥ ድል ያጎናፀፈን ፈጣሪን እያመሰገንን በፅናት መቆም ይገባናል - የቤተክርስቲያን አባቶች
ሀዋሳ፣ ሐምሌ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በፈተና ውስጥ ድል ያጎናፀፈን ፈጣሪን እያመሰገንን የሚገጥሙንን መሰናክሎች ለማለፍ በአንድነትና በፅናት ልንቆም ይገባናል ሲሉ በሀዋሳ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን አባቶች ተናገሩ ።
የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ኢትዮጵያ ሰበካ በሀዋሳ ከተማ አቀፍ የ"ኢትዮጵያ ታመስግን" የምስጋናና ፀሎት መርሀ ግብር አከናውነዋል ።
ምስጋና ለፈጣሪና በአጠገባችን መልካም ለሰሩት መስጠት ለተሻለ ድልና ሃላፊነት ማዘጋጀት መሆኑን የገለጹት ምዕመናኑ ምድር ላይ እስካለን ፈተና የማይጠፋ በመሆኑ የሚገጥሙንን ፈተናዎች ለመሻገር አንድነትና ጽናት የሚጠበቅ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የሰበካው የሥራ መሪ የሆኑት ፓስተር ዳንኤል ዶያሞ እንደ ሀገር ማለፍ የከበዱንን ፈተናዎች ሁሉ በኃይሉ እያሻገረ ለዚህ ያደረሰንን እግዚአብሔርን ማመስገን ተገቢ ነው ብለዋል ።
ፈተናዎቻችን ከሚያስከትሉት ጉዳት ባሻገር ለጥንካሬና ብርታታችን መነሻም እንደሚሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል ያሉት ፓስተር ዳንኤል ኢትዮጵያ ያለፈቻቸው የጭንቅ ጊዜያት በጨለማ ውስጥ የነገን ብርሀን አሻግሮ ማየት እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ እንደሆነ ጠቅሰዋል ።
በመሆኑም በፈተና ውስጥ ድል ያጎናፀፈን እግዚአብሔርን እያመሰገንን የሚገጥሙንን መሰናክሎች ለማለፍ በአንድነትና በፅናት መቆም ይገባናል ብለዋል ።
ከሰሞኑ በዓለም አደባባይ ኢትዮጵያንና ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ ያደረጉ አትሌቶቻችን መተባበርና ፍቅር ከተላበስን በፈተና ውስጥም ከፊት የሚጠብቀን ድል እንዳለ አሳይተውናል ነው ያሉት ።
ኢትዮጵያውያን በአምልኮ ስፍራ፣ በዕለት ተለት መስተጋብራችንና በሠላምታችን አመስጋኝና ፀሎተኞች በመሆናችን አምላካችን ጠብቆናል እርዳታው ተለይቶን አያውቅም ያሉት ደግሞ የመናኸሪያ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን ሽማግሌና የአውራጃ ኮሚቴ አባል አቶ አሰፋ ኢቲሶ ናቸው።
ምስጋናና ፀሎት ካለ ሁሌም ድል አለ ያሉት አቶ አሰፋ ኢትዮጵያውያን ዓለምን ያስጨነቀው የኮሮና ወረርሽኝ አስከፊ ጉዳት ሳያስከትል ያለፍነው በፈጣሪ እርዳታ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በነበረው ዓለም አቀፍ ጫና ምክንያት ሳይቋረጥ ግንባታው መቀጠሉና በከፊል ኃይል ማመንጨት መጀመሩ በሀገራችን የምስጋና፣ የፀሎትና በህብረት የመቆም ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል ።
ወንድምን በወንድም ላይ የሚያስጨክን የሰይጣን አሰራርና ግፍ እያስተናገድንም ቢሆን ኢትዮጵያዊያን በአንድነታቸው ፀንተው መቆማቸውም እንዲሁ በአምላክ ቸርነት የተጎናፀፍነው ድል ነው ብለዋል ።
ኢትዮጵያ ሊነጋላት ሲል እንዲጨልምባት የሚያደርጉ ፈተናዎች ዛሬም ቢቀጥሉም አሁንም እጆቿን ወደ እግዚአብሔር መዘርጋቷን አጠናክራ መቀጠል አለባት ነው ያሉት ።
ከፊት ያሉ ፈተናዎችንም በድል ለመወጣት በፈጣሪ ፊት መንበርከክና በህብረት መቆም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል ።
በሀዋሳ ጊምቤ ሞኖፖል የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን ውስጥ በተካሄደው መርሀ ግብር ላይ የሰበካው መሪዎች፣ የአብያተክርስቲያን ሽማግሌዎች እና በርካታ ምዕመናን ታድመዋል ።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ