የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከህዝባዊ አገልግሎቱ በተጓዳኝ ለአገራዊ ልማትና ማህበራዊ ሃላፊነት በልዩ ትኩረት ይሰራል- የባንኩ ፕሬዝዳንት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከህዝባዊ አገልግሎቱ በተጓዳኝ ለአገራዊ ልማትና ማህበራዊ ሃላፊነት በልዩ ትኩረት ይሰራል- የባንኩ ፕሬዝዳንት
ሐምሌ 23 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከህዝባዊ አገልግሎቱ በተጓዳኝ ለአገራዊ ልማትና ማህበራዊ ሃላፊነት በልዩ ትኩረት መስራቱን ይቀጥላል ሲሉ የባንኩ ፕሬዝደንት አቤ ሳኖ ተናገሩ።
የባንኩ ሰራተኞችና የማኔጅመንት አባላት 4ኛውን ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በማስመልከት ችግኝ ተክለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የባንኩን ፕሬዝደንት አቤ ሳኖን ጨምሮ ሌሎችም የተገኙ ሲሆን ችግኝ ከመትከላቸው ቀደም ብለው በ"ኢትዮጵያ ታመስግን" ጥሪ መሰረት የምስጋና ስነ ስርአት አከናውነዋል።
በመቀጠልም የባንኩ ሰራተኞችና የማኔጅመንት አባላቱ በለሚኩራ ክፍለ ከተማ ጸሀይ ሪል እስቴት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ችግኞችን ተክለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝደንት አቤ ሳኖ፤ የአካባቢ መራቆት አየር ንብረት ለውጥ መዛባትን በማስከተል ብዙ ዋጋ እያስከፈለ በመሆኑ ለአረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት አመታት የአረንጓዴ ልማት በስፋት መከናወኑን አስታውሰው ባንኩም ከሁለት ሚልየን በላይ ችግኞችን መትከሉን ጠቅሰዋል።
የባንኩ አመራርና ሰራተኞች በዘንድሮው አመትም ከ500 ሺህ በላይ ተጨማሪ ችግኞችን ለመትከል እቅድ መያዛቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከህዝባዊ አገልግሎቱ በተጓዳኝ ለአገራዊ ልማትና ማህበራዊ ሃላፊነት በልዩ ትኩረት መስራቱን ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።
በእለቱ ችግኝ ከተከሉት መካከል ያነጋገርናቸው የባንኩ ሰራተኞች ህዝብን ከማገልገል ባለፈ በአገራችን ልማት ተሳታፊ በመሆናችን ተደስተናል ብለዋል።
በቀጣይም የተተከሉ ችግኞችን በቅርበት በመንከባከብ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር "ዐሻራችን ለትውልዳችን" በሚል መሪ ሃሳብ እየተከናወነ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ እስካሁን 5 ቢሊዮች ችግኞች መተከላቸው ይታወቃል።