ቀጥታ፡

"አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የምክክር ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንጂ የማደራደር ስልጣን የለውም"-የኮሚሽኑ ሰብሳቢ

ሐምሌ 23 ቀን 2014(ኢዜአ) "የአገራዊ ምክከር ኮሚሽን ኅላፊነት በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የምክክር መድረክ ማመቻቸት እንጂ የማደራደር ስልጣን የለውም " ሲሉ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ተናገሩ።

ኮሚሽኑ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ገቢራዊ በሚያደርገው ስትራቴጂክ እቅድ ዙሪያ ከመገናኛ ብዙሃን፣ ሰላም ሚኒስቴር፣ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ከባለድርሻ ሲቪክ ተቋማት ተወካዮች ጋር ተወያይቷል።

ምክክር ኮሚሽኑ የተቋቋመው በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ በተፈጠሩ ልዩነቶች በውይይት ዘላቂ ዕልባት መስጠት የሚያስችሉ ህዝባዊ ምክክሮችን በማካሄድ ችግሮችን ለይቶ በጥናት የተደገፈ መፍትሄ ለማመላከት ነው።

ለዚህም አካታችና አሳታፊ፣ ገለልተኛ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት፣ ትብብር፣ ሕጋዊነትና ተዓማኒነትን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑም የምክክር ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፈሰር መስፍን አርዓያ ገልፀዋል።

ኮሚሽኑ ግቡን ለማሳካት ይረዳው ዘንድ ስትራቴጂካዊ እቅድ ማዘጋጀቱን ገልጸው፤ ለምክክሩ ውጤታማነትም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በምክክር ሂደቱ አጀንዳ የመቅረጽ ኅላፊነት ለህዝብ የተተወ መሆኑን ገልፀው፤ ኮሚሽኑ የህዝብ አጀንዳዎች ተቀባይነት እንዲያገኙ ይሰራል እንጂ የህዝቡ አጀንዳ የመቅረጽ ኅላፊነት እንዳልተሰጠው ተናግረዋል።

አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የውይይት ሂደቶችን ማመቻቸት እንጂ የማደራደር ስልጣን የለውም ብለዋል።

በተሰጠው ማብራሪያ ላይ ተሳታፊዎች ቢካተቱ በሚሏቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳብ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አገሪቷ ያለፈችበትን ውጣ ውረድ በቅርበት እንደሚያውቁ በመግለጽ ሚዲያዎችን ማሳተፍ ለምክክሩ ስኬት የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቁሟል።

May be an image of 1 person and standing

ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን የተወከሉት አቶ ጌቱ ሙላቱ፤ ምክክር ኮሚሽኑ የአካል ጉዳተኞችን ማሳተፍ ላይ የበለጠ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።

የአካል ጉዳተኝነት በዓይነትም፣ በአደረጃጀትም የተለያዩ በመሆናቸው ኮሚሽኑ ይህን ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሁኔታዎችን እንዲያመቻችም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተወካይ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ በበኩላቸው ኮሚሽኑ በምክክር ላይ የቀደመ ልምድ ካላቸው ተቋማት ጋር ተቀራርቦ መስራት እንዳለበት አንስተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም