የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት በዓለም የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ የፈጠረው መስተጓጎል ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ አገራት የማንቂያ ደወል ነው - ዶክተር ፍጹም አሰፋ - ኢዜአ አማርኛ
የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት በዓለም የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ የፈጠረው መስተጓጎል ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ አገራት የማንቂያ ደወል ነው - ዶክተር ፍጹም አሰፋ
ሐምሌ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) “የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት በዓለም የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ የፈጠረው መስተጓጎል ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገራት ራሳቸውን በምግብ እንዲችሉ የሚያሳስብ የማንቂያ ደወል ነው” ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።
በአፍሪካ ዓለም አቀፍ ድንገኛ ክስተቶች የሚያመጡትን ጫና የሚቋቋም የኢኮኖሚ አቅም መገንባት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም በሲኤንኤን የቴሊቪዥን ጣቢያ “ኴስት ሚንስ ቢዝነስ” በተሰኘው ፕሮግራም ላይ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አስመልክቶ ከጋዜጠኛ እሌኒ ጊዮኮስ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም የምርት አቅርቦት ሰንሰለት ላይ በፈጠረው መረበሽ ኢትዮጵያ በዋጋ በኩል ከውጭ የምታስገባቸው ዘይት፣ ነዳጅ፣ ማዳበሪያ እና ሌሎች ምርቶች ላይ የታየው ከፍተኛ ጭማሪ ተጽእኖ እንዳሳደረባት ዶክተር ፍጹም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከውጭ አገር የምታስመጣው ማዳበሪያ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሬ ጫና እንደፈጠረ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እየጨመረ ላለው የዋጋ ንረት የራሱ የሆነ ተጽእኖ እንዳሳረፈም አመልክተዋል።
“የኢትዮጵያ ዋጋ ንረት ችግር የቅርብ ጊዜ ክስተት አይደለም፤ ለረጅም ጊዜ የቆየና በዝቅተኛ ምርታማነት እንዲሁም ተወዳዳሪነት ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል” ብለዋል።
ለዋጋ ንረቱ መፍትሔ ለማበጀት መንግስት የተለያዩ ማሻሻያዎች በማድረግ እና የ10 ዓመት የመሪ ልማት እቅድ አዘጋጅቶ ኢኮኖሚው ተወዳዳሪና ምርታማ እንዲሆን እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሁሉን አቀፍ የሆነ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መገባቱን ገልጸው፤ በማሻሻያው የኢኮኖሚ እድገቱን ለመጨመር እና ጫናዎችን የሚቋቋም ኢኮኖሚ ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በዚህ ረገድም በግብርናው ዘርፍ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ ምርታማነትን የመጨመር እንዲሁም የግብርና ማቀነባባሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን አመልክተዋል።
በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት አማካኝነት ከፍተኛ ምርት መገኘቱን የኢኮኖሚ ጫናዎችን ለመቋቋም አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ገልጸዋል።
በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተው ጦርነት በኢኮኖሚው ላይ ተጽእኖ ቢያደርግም መንግስት ያደረጋቸው ሁሉን አቀፍ ማሻሻያዎች ኢኮኖሚው በታሰበው እንዲጓዝ አድርጓል ብለዋል።
የአፍሪካ አገራት ወደ ውስጣቸው በማየት ያለውን ሀብት መጠቀምና የአየር ንብረት ለውጥ የፈጠራቸውን ፈተናዎች የሚቋቋምና የሚቀንስ ስትራቴጂ መቀየስ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ማዳበሪያን አገር ውስጥ ባሉ ግብአቶች በማምረት ከውጭ የሚገባውን ለማስቀረት እንቅስቃሴ መጀመሯን ጠቁመዋል።