ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተጠናቀቀው በጀት አመት 10 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱን ገለጸ

ሀምሌ 23/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተጠናቀቀው በጀት አመት 10 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱን ገለጸ።

የባንኩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፉት ሶስት አመታት በተለይም በሪፎርም ስራዎች ላይ በስፋት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው በጀት አመት ባንኩ 19 ቢሊዮን ብር ብድር የማጽደቅ እቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም ከእቅዱ በላይ ማጽደቅ መቻሉንም አስታውሰዋል።

በ2013 በጀት አመት ባንኩ ጥራት ላይ በማተኮር መስራቱ ለተጠናቀቀው በጀት አመት መሰረት የጣለ አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

በዚህም በ2013 በጀት አመት 10 ቢሊዮን ብር ብድር ሲያጸድቅ በ2014 በጀት አመት ደግሞ 19 ቢሊዮን ብር ለማድረስ አቅዶ መስራቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም በ2014 በጀት አመት ከፈቀደው 22 ቢሊዮን ብር ብድር 10 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለተበዳሪዎች መስጠቱን ዶክተር ዮሐንስ ተናግረዋል።

የባንኩ የአሰራር ማሻሻያ በደንበኞች ዘንድ እምነት በመፍጠር እና በቅርበት በመስራት ውጤታማ መሆኑን አስታውሰዋል።

በ2015 በጀት አመትም አሰራሩን ይበልጥ በማዘመንና በማሻሻል የሚሰጠውን ብድር 30 ቢሊዮን በማድረስ ለማፅደቅ ማቀዱን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም