ቀጥታ፡

አየር መንገዱ የአየር ብክለትን ለመቀነስ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ያላቸውን አውሮፕላኖች ስራ ላይ እያዋለ ነው

ሐምሌ 23 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ፤ የአየር ብክለትን ለመቀነስ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ያላቸውን አውሮፕላኖች ስራ ላይ እያዋለ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው መስፍን ጣሰው ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞችና አመራሮች በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 አካባቢ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር አካሄደዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፤ አየር መንገዱ ከተሰጠው ዋና ተልዕኮ በተጨማሪ በአገራዊ ልማትና ማህበራዊ ሃላፊነቶች ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል።

ከልማት አንፃር በተለይም በአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር ባለፉት ሶስት ዓመታት ጠንካራ ተሳትፎ ማድረጉን አስታውሰው ዘንድሮም መቀጠሉን ተናግረዋል።

በዘንድሮው ዓመት ከ100 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

አየር መንገዱ ከአረንጓዴ ልማት ተሳትፎው በተጨማሪ በበረራው ዘርፍ ሊፈጠር የሚችለውን የአየር ብክለትን ለመቀነስ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ያላቸውን አውሮፕላኖች ስራ ላይ እያዋለ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን እውን ለማድረግ ችግኞችን መትከል ብቻ በቂ ባለመሆኑ ተንከባክቦ ማልማት ያስፈልጋል ብለዋል።

የአየር መንገዱ ሰራተኛ አቶ አገሬ አሰፋ፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ችግኞችን መትከልና እንዲፀድቁ ሁላችንም መንከባከብ ይጠበቅብናል ብለዋል።

May be an image of 9 people, people standing and outdoors

ሌላኛዋ የአየር መንገዱ ሰራተኛ ወይዘሮ ኤልሳ ቤተማሪያም፤ ችግኞች ፀድቀው ለተፈለገው አላማ እንዲውሉ ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመንከባከብ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

በአየር መንገዱ ሰልጣኝ ፓይለት አቤል ወርቁ፤ ችግኞችን ከመትከል ባሻገር እንክብካቤ ላይ ትኩረት ስጥቶ መስራት የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብሏል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም