ቀጥታ፡

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ስለሺ በቀለ ከአሜሪካ ሕግ አውጭዎች ጋር ተወያዩ

ሐምሌ 23 ቀን 2014(ኢዜአ) በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከአሜሪካ የሕግ አውጭ ምክር ቤት አባላት ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አደረጉ።

አምባሳደር ስለሺ ባለፉት ጥቂት ቀናት ከሴናተር ቴድ ክሩዝ(ፍሎሪዳ) እንዲሁም ከኮንግረስ አባላቱ ዳሬል ኢሳ(ካሊፎርንኒያ)፣ጁሊያ ሌትሎው (ሉዊዚያና)፣ክሪስ ስሚዝ(ኒው ጀርዚ)፣ስቲቭ ዎማክ(አርካንሳስ) እና ቻክ ፍሌሽማን(ቴነሲ) ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በግጭት እና በድርቅ ምክንያት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን ገልጸዋል።

ሰላምን ለማስፈን እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች፣የማህበራዊ እና ኢኮኖሚ ልማት ስራዎች፣የዴሞክራሲ ሂደት፣የአልሸባብ የሽብር ቡድን በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለማድረስ ያደረገውን ሙከራና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ለሕግ አውጪዎቹ ማብራሪያ መስጠታቸው ተመልክቷል።

በተጨማሪም አምባሳደሩ የ”ኤችአር 6600” እና የ”ኤስ 3199” ረቂቅ ሕጎች ያላቸውን ስጋት የገለጹ ሲሆን “ሕጎቹ የሚጸድቁ ከሆነ ለረጅም ጊዜ የቆየው የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት እንዲሁም አሁን በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ አበረታች ለውጦች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ የእድገትና ዕድል ድንጋጌ(አጎዋ) መውጣቷ መደበኛ ዜጎች ላይ እየጎዳ እንደሚገኝና የሕግ አውጪ ምክር ቤት አባላቱ ኢትዮጵያ ወደ ተጠቃሚነቷ እንድትመለስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የሕግ አውጪዎቹ በውይይቱ ላይ በሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት፣ሰላም ለማምጣት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች እና የምክክር ሂደቱ ላይ መልካም የሚባሉ ለውጦች እንዳዩ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ኢትዮጵያና አሜሪካ ያላቸውን ታሪካዊ ትብብር ማጠናከር ያለውን ፋይዳ ወሳኝ መሆኑን እንዲሁም በአገራቱ ግንኙነት መካከል ያሉ ክፍተቶች መፍትሔ እንዲመጣ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ መናገራቸው ተገልጿል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ስለሺ በቀለ በቅርቡ ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሀመር፣ የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ጂም ሃይምስ(ኮኔቲከት) እና ጆን ጋራሜንዲ(ካሊፎርኒያ) እንዲሁም ከሴናተር ጂም ኢንሆፌ(ኦክላሃማ) ጋር ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም