ኢህአዴግ የአመራር ለውጥን ተከትሎ የተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች ህዝባዊና ህገ-መንግስታዊ መሆናቸውን አረጋገጠ - ኢዜአ አማርኛ
ኢህአዴግ የአመራር ለውጥን ተከትሎ የተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች ህዝባዊና ህገ-መንግስታዊ መሆናቸውን አረጋገጠ

አዲስ አበባ መስከረም 5/2011 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በመጋቢት ባካሄደው ስብሰባ የተላለፉ ውሳኔዎች እና የአመራር ለውጥን ተከትሎ የተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች ህዝባዊ፣ ህገ-መንግስታዊ እና የድርጅቱን መርሆዎች የተከተሉ መሆናቸውን ምክር ቤቱ አረጋግጠ፡፡ የኢህአዴግ ምክር ቤት ከመስከረም 4 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ ማምሻውን አጠናቋል። ምክር ቤቱ 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ከመስከረም 23 እስከ 25 ቀን 2011ዓ.ም እንዲካሄድም ወስኗል። የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ፖለቲካዊ መረጋጋት የማምጣት፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ አለመግባባትን ወደ ሰላማዊ መስመር የመመለስ፣ ዳያስፖራውን በአገር ጉዳይ ላይ እንዲሳተፍ የማድረግ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ እና በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል አንድነትን ለማጠናከር የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ገምግሟል። ኢትዮጵያ ውሰጥ የተለያየ የፖለቲካ አቋም ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማቅረብ የሚችሉበት የፖለቲካ ምህዳር መፈጠሩ በኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር መሰረት መጣሉን አመልክቷል። በኢኮኖሚው መስክ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማቃለል፣ የዋጋ ንረትን ለመግታት፣ ህገ-ወጥ ንግድን እና የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር እንዲሁም ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የተሰሩ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የገመገመ ሲሆን፤ ለወደፊቱም አቅጣጫ አስቀምጧል። በወጪ ንግድ መስክ የሚታየው ዝቅተኛ አፈፃፀም የውጭ ምንዛሪ እጥረት መኖሩ፣ የውጭ ብድር የመክፈል አቅም እየተዳከመ መምጣት፣ የገቢ አሰባሰብ ዝቅተኛ ሆኖ መቆየት፣ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ችግሮችን ለማቃለል ከፍተኛ ርብርብ መደረግ እንዳለበትም በጥልቀት ተወያይቷል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማቃለልም ሆነ የዜጎችን ተጠቃሚነት በማሳደግ አገራዊ ዕድገቱን ለማስቀጠል ምርታማነትን ለማሻሻል አስፈላጊነትን ያመለከተው መግለጫው፤ በኢንዱስትሪና በግብርና መስክ መሻሻል የሚፈልጉትን ጉዳዮች በተመለከተ በተከታታይ እየለዩ ማሻሻል በሚቻልባቸው አቅጣጫዎች ላይ ተወያይቷል። የዲሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር፣ የፌደራል ሥርዓቱን ብሔረሰባዊና ኢትዮጵያዊ ማንነትን አስማምቶ በመሄድ ረገድ የሚያጋጥሙ የአመለካከትም ይሁን መዋቅራዊ ችግሮችን ማቃለል እንደሚገባና ተከታታይ የለውጥ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ የግንባሩ ምክር ቤት ህዝቡ የህግ የበላይነት እንዲከበር በፅናት እንዲታገልና ለውጡን ጠብቆ እንዲያስቀጥል ጥሪውን አቅርቧል፡፡ ለውጡን በብቃት የመምራት አስፈላጊነትን አስመልክቶ ባደረገው ውይይት የለውጡን ገፊ ምክንያቶች በመመርመር ዘላቂ ተቋማዊ ብቃት መገንባት እንደሚገባ ጠቁሞ፤ ለውጡ ተቋማዊና ህጋዊ ማዕቀፍ ይዞ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ የፖለቲካ ማሻሻያዎች የኢህአዴግ የውስጠ ድርጅት ሪፎርም፣ አስተዳደራዊ ሪፎርም እና የህግ ሪፎርም የማካሄድ አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ደርሷል፡፡ የድርጅቱን ተራማጅነት፣ ውስጣዊ አንድነት፣ አንፃራዊ ነፃነትና የአሰራር ምቹነት ለማጎልበት ሊሰራ እንደሚገባ ያመለከተው የምክር ቤቱ መግለጫ፤ ጠንካራና መልካም የመንግስት አስተዳደር ለመፍጠር ያልተማከለና ለዘርፉ ልዩ ባህሪ ትኩረት በመስጠት የፍትህ ተቋማት፣ የምርጫ ቦርድና የደህንነት ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ ለማድረግ የሚያስችል ማሻሻያ እንዲካሄድ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ የመደመር ፅንሰ ሀሳብ ላይ የመከረው ምክር ቤቱ "ጽንሰ ሀሳቡ ከድርጅቱ መርሆዎችና እሴቶች ጋር የተጣጣመ ይልቁንም አገራዊ ይዘትና ፋይዳ ያለው የሰላም፣ የፍቅርና የይቅርታ እሳቤ መሆኑን በማመን እንዲበለፅግ፣ ህዝቡ በሙሉ ፍላጎቱ እንዲያውቀው፣ እንዲያሰፋውና የለውጥ መርሆዎቹን ተገንዝቦ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ተሳትፎ" ለማድረግ እንዲችል የተለያዩ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው ከመግባባት ላይ ደርሷል። ‹‹አገራዊ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ለውጥ!›› በሚል መሪ ሃሳብ በመስከረም መጨረሻ ለሚካሄደው 11ኛው ጉባዔ የሚቀርቡ አቅጣጫዎች ላይ መክሯል፡፡ ምክር ቤቱ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የግማሽ ዘመን አፈፃፀም በመገምገም የቀሪውን ጊዜ የትኩረት አቅጣጫዎች አስቀምጧል። የተጀመረውን ቀጣይነት ያለው ዕድገት አጠናክሮ በማስቀጠል ድርጅትና ፖለቲካ፣ በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ በለውጥና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት መስክ የተቀመጡትን የቀጣይ ዓመታት አቅጣጫዎችን በዝርዝር ፈትሾ በማዳበር አፅድቋል፡፡ ምክር ቤቱ በደቡብ ክልል በሃዋሳ የሚካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ በስኬት እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ መቀመጡን የገለጸው መግለጫው፤ የቀሪ ጊዚያት የዝግጅት ሥራዎች እንዲጠናቀቁ አጽንኦት ሰጥቷል።