የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኤ350-1000 ሞዴል ኤርባስአውሮፕላኖችን በመግዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኤ350-1000 ሞዴል ኤርባስአውሮፕላኖችን በመግዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ ሆነ
ሐምሌ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንግድ የኤ350-1000 ሞዴል ኤርባስ አውሮፕላኖችን በመግዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኑን የኤርባስ ኩባንያ አስታወቀ።
አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም የኤ350-900 ሞዴል የሆኑ 22 ኤርባስ አውሮፕላኖችን ግዢ የፈጸመ ሲሆን አሁን ደግሞ አራት የኤ350-1000 ሞዴል እና ሁለት የኤ350-900 ሞዴል አውሮፕላኖችን ግዢ በመፈፀም በአፍሪካ ቀዳሚው አየር መንገድ ነው ሲል ኤርባስ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንዳሉት፤ ለአፍሪካ የመጀመሪያ የሆኑት የኤ350-1000 ሞዴል ኤርባስ አውሮፕላኖች አየር መንገዱን ከአፍሪካ በቴክኖሎጂ መሪ እንዲሆን ያስችሉታል።
የኤ350-1000 ሞዴል ኤርባሶች የነዳጅ ፍጆታቸው አነስተኛ፣ እጅግ ዘመናዊ የሆኑና እያደገ የመጣውን የደንበኞችን ፍላጎት ማርካት የሚችሉ መሆናቸውን ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
አየር መንገዱ እራሱን ዘመኑ ከደረሰበት የቴክኖሎጂ እድገት ጋር በማዋሃድ፣ ቀልጣፋ፣ ምቹ እና ተመራጭ የሆኑ አገልግሎቶችን ለደንበኞች መስጠት እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በኤርባስ ኩባንያ የአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ፕሬዝዳንት ሚካል ሆአሪ በበኩላቸው የኤ350-1000 ሞዴል ኤርባስ አውሮፕላን በአለም እጅግ ቀልጣፋ፣ በቴክኖሎጂ የበለፀገ፣ ትልቁ የመንገደኞች አውሮፕላን ነው ብለዋል።
አየር መንገዱ ይሄንን ዘመናዊ አውሮፕላን መግዛቱ በአቪዬሽን ዘርፉ ከአህጉሪቱ መሪነቱን ይዞ እንዲቀጥል የሚያደርገው መሆኑን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም የገዛቸው የኤ350-900 ኤርባስ አውሮፕላኖች የላቀ አቅም ያላቸው፣ ነዳጅ ቆጣቢ የሆኑ፣ 99 ነጥብ 5 በመቶ አስተማማኝ የሆኑ፣ የማይበገሩ፣ ቀልጣፋ፣ ከረጅም እስከ ቅርብ ርቀት በመጓዝ ተለዋዋጭ የሆነ አገልግሎትን መስጠት የሚችሉ እንደሆኑ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የኤ350-900 ሞዴል ኤርባስ አውሮፕላኖች እ.አ.አ በ2015 ወደ ገበያው የገቡ ሲሆን የኤ350-1000 አውሮፕላኖች ደግሞ ወደ ገበያው የገቡት እ.አ.አ በ2018 ነው።