ቀጥታ፡

ባለፉት ስድስት ወራት ለ126 ሰዎች የተሳካ የዓይን ብሌን ንቅለ-ተከላ ተደርጓል

ሀምሌ 22/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ ለ126 ሰዎች የተሳካ የዓይን ብሌን ንቅለ-ተከላ መደረጉን የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ አስታወቀ።

ባንኩ የዓይን ብሌን ልገሳ ባህል እንዲዳብር የዓይን ብሌን ንቅለ-ተከላ ማኅበር ለማቋቋም በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ የግንዛቤ ፈጠራ አስተባባሪ አቶ ነጋ ደምሴ እንደገለጹት፤ የዓይን ባንኩ ዋና ዓላማ ሊድን በሚችል የዓይን ብሌን ጠባሳ የሚመጣ ማየት አለመቻልን ማከም ነው።

ባንኩ በሕይወት እያሉ ቃል ከገቡ ሰዎች የዓይን ብሌን በማሰባሰብ ንቅለ-ተከላውን ለሚያከናውኑ የሕክምና ተቋማት ማሰራጨቱን ተናግረዋል።  

አስተባባሪው የዓይን ብሌን ጠባሳ የሰው ልጆችን ሙሉ ለሙሉ ማየት የተሳናቸው ሊያደርግ እንደሚችል ገልጸው፤ ሕክምና ካገኙ ሊድኑ እንደሚችሉ አመልክተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራትም ለ126 ዜጎች የተሳካ የዓይን ብሌን ንቅለ-ተከላ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በዓይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት የሚከሰተውን ዓይነ-ስውርነት ለማጥፋት የዓይን ብሌን የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ባንኩ ይህን ያድርግ እንጂ እንደ አገር በፍላጎት እና አቅርቦት መካከል ያለው ልዩነት ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ በቀዳሚነት የሚነሳው ሕብረተሰቡ ስለ ዓይን ብሌን ንቅለ-ተከላ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑን አመልክተዋል።

አቶ ነጋ በዓይን ብሌን ልገሳ ዙሪያ የሚስተዋለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የዓይን ባንክ ማኅበር ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ማኅበሩ ከዚህ በፊት በተደረገላቸው ሕክምና ካለማየት ወደ ማየት የመጡ ወገኖችን የሚያቅፍ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

እነዚህ ወገኖች ደግሞ የተደረገላቸውን ሕክምና ለሕብረተሰቡ በተግባር በማሳየት የዓይን ብሌን ልገሳ ባህል እንዲያድግ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ የሚያከናውኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ድረስ የዓይን ብሌን ንቅለ-ተከላ የሚደረገውም ሆነ የሚሰበሰበው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ነጋ፤ በቀጣይ ግን በክልሎች ጭምር የሚሰራበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የዓይን ጠባሳ ሊድን የሚችለው ሰዎች ከህልፈታቸው በኋላ በሚለግሱት የዓይን ብሌን በመሆኑ፤ ሰዎች ከማለፋቸው በፊት የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ባለፉት 19 ዓመታት ለ2 ሺህ 860 ኢትዮጵያዊያን የተሳካ የዓይን ብሌን ንቅለ-ተከላ አካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም