ኢዜአ በሀገር ገፅታ ግንባታና በህልውና ዘመቻ የተጣራ መረጃ በማድረስ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ በሀገር ገፅታ ግንባታና በህልውና ዘመቻ የተጣራ መረጃ በማድረስ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው - ቋሚ ኮሚቴው
ሐምሌ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በሀገር ገፅታ ግንባታ፣ በሉዓላዊነትና በህልውና ዘመቻው ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭው ዓለም ማህበረሰብ የተጣራ መረጃ በማድረስ ረገድ የነበረው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢዜአን የ2014 ዓ.ም የስራ አፈፃፀምና የ2015 መሪ እቅድን ዛሬ በአዳማ ገምግሟል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ ኢዜአ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣትና ያስቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት እያከናወነ ያለው ተቋማዊ ግንባታና ሪፎርም አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢዜአ እውነተኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ዓላም አቀፉ ማህበረሰብ የተዛባ ግንዛቤ እንዳይኖረውና ከውጭ ሚዲያዎች ጭምር በሃገር ላይ የተከፈተውን ሐሰተኛ መረጃ የማክሸፍ ስራ ሰርቷል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተቋሙ የሪፎርምና ይዘት ስራዎች ጥሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በቋሚ ኮሚቴው የመገናኛ ብዙሃን ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አቡኔ ዓለም ናቸው።
ቋሚ ኮሚቴው ተቋሙ በድረ ገጽና ዩቲዩብ ተደራሽነት አንፃር የነበረውን ውስንነት በመቅረፍ ለአዲሱ የበጀት ዓመት የተሻለ ስራ ለመስራት የሚያስችል የ2015 ዓ.ም መሪ እቅድ መዘጋጀቱንም በዝርዝር ተመልክቷል ነው ያሉት።
ተቋሙን ገቢ ከማሳደግ፣ ከሰው ሃይል ክህሎት፣ እውቀትና አመለካከት ልማት አንፃር ተቋሙ ከአፍሪካ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን ያስቀመጠውን ግብና ራዕይ ለማሳካት የሚያስችሉት አሰራሮችና የህግ ማዕቀፎች ሊኖሩት እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ ተናግረዋል።
የኢዜአ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው ተቋሙ እያከናወነ ካለው ተቋማዊ ግንባታና ሪፎርም በሻገር ተደራሽነትን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ለማስፋት እየሰራ ይገኛል።
የአሰራር፣ የተጠያቂነት፣ የህግና የአደረጃጀት ክፍተቶችን ለማስተካከል ረቅቅ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።
ተቋሙ የዩቲብ የገቢ አቅም ለማሳደግና ቅርንጫፎችን በቁሳቁስ የማጠናከር ስራ ይሰራል ብለዋል።