የአባቶቻችን የድል ምስጢር በጀግኖች አትሌቶች ተደግሟል ሲሉ የነገሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የአባቶቻችን የድል ምስጢር በጀግኖች አትሌቶች ተደግሟል ሲሉ የነገሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ
ነገሌ እና ነቀምቴ ሐምሌ 21/2014--- ጀግኖች አባቶቻችን አንድነታቸውን አጠናክረው በአድዋ ድል ያገኙበት ምስጢር ዛሬም በዓለም አደባባይ በአትሌቶቻችን ተደግሟል ሲሉ የነገሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው የኢትዮጵያ የአሸናፊነት ክብር ዛሬም በጀግኖች አትሌቶቿ መቀጠሉን በዓለም መድረክ ተመስክሯል ብለዋል።
ኢትዮጵያን ወክሎ በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፈው የአትሌቲክስ ቡድን ልዑክ ለተደረገውን ደማቅ አቀባበል የነገሌ ከተማ ነዋሪዎች የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
የከተማው ነዋሪ አቶ ደስታ ቡቸና እንዳሉት ድሉ የሁሉም በመሆኑ ክብር፣ ኩራትና ደስታ ተሰምቷቸዋል።
ጀግኖች አባቶቻችን በአክሱምና በላልይበላ ድንጋይ ፈልፍለው፣ ተራራ አንጸው ህንጻ በመስራት ባሳዩት ጥበብ ኢትዮጵያ ከዓለም በስልጣኔ ቀደሚ እንደነበረች አስታውሰዋል።
"በአንድነትና በመረዳዳት በአድዋ ጦርነት በአባቶቻችን ድል የተመዘገበበት ምስጢር ዛሬም በዓለም አደባባይ በአትሌቶቻችን ተደግሟል" ብለዋል።
በከተማው የቀበሌ 03 ነዋሪ አቶ ገመዳ ቡሳዋ በበኩላቸው "በአትሌቲክሱ የተገኘው ውጤት እንደአደዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው አፍሪካ ኩራት ነው" ብለዋል።
"ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ደምቃ በታየችበት 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተገኘው ድል ከማሸነፍ በላይ ለእኛ ልዩ ትርጉም ስላለው ደስታዬ እጥፍ ድርብ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።
አቶ ሶራ ገልገሎ የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው፣ መደጋገፍና መረዳዳት ለውጤት እንደሚያበቃ ከአትሌቶቹ በተግባር ማየታቸውን ገልጸዋል።
"እርስ በርስ ከተባበርንና ከተረዳዳን እኛም ተጨማሪ ድል ማስመዝገብ እንደምንችል የአትሌቲክሱ ውጤት ጥሩ ማሳያ ነው" ብለዋል።
ጀግኖች አባቶች ሀገር ያጸኑበትን ምስጢርን ዛሬም አትሌቶቻችን በዓለም አደባባይ ደግመው የኢትዮጵያዊያንን የቆየ አንድነት ባህል ለዓለም ማስመስከራቸውንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አትሌዮች ለሀገር ቅድሚያ በመስጠት በመረዳዳትና በመተጋገዝ ባመጡት ውጤት ኩራትና ደስታ እንደተሰማቸውም ተናግረዋል።
የጉጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብዱረዛቅ ሁሴን በበኩላቸው፣ "አትሌቶቹ በዓለም አደባባይ ኢትዮጵያን ያጎሉበትን ምስጢር ተረድተን እኛም በልማት ሀገርን ከፍ ለማድረግ እንስራ" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከጥንት አባቶቻችን ጀምሮ የአንድነት፣ የመቻቻል፣ የሰላም፣ የልማትና የአሸናፊነት ተምሳሌት ሀገር እንደሆነች ታሪክ ያስረዳል ሲሉም ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ዜና የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ የአሸናፊነት ክብር ዛሬም በጀግኖች አትሌቶቿ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ድሉ ሀገር በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆናም አኘናፊነቷን በተጨባጭ ያስመሰከረ መሆኑንም ተናግረዋል።
የነቀምቴ ከተማ ነዋሪና የጉቶ ጊዳ ወረዳ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ እውነቱ እንዳሉት፣ አትሌቶቹ ሀገርን በማስቀደምና በመደጋገፋቸው ውጤት አምጥተዋል።
"ኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ብትሆንም ፈተናዎቹን እያለፈች ወደነበረችበት የከፍታ ማማ እየገሰገሰች መሆኗን በተግባር አሳይተዋል፤ በእዚህም ሊመሰገኑ ይገባል" ብለዋል።
"በህብረት ከተሰራ ታሸንፋለህ፣ አንዱ ለሌላው ጉልበት ይሆናል" ያሉት ደግሞ የጉቶ ጊዳ ወረዳ የገቢዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቀደ ለሚ ናቸው።
"ጀግኖች አትሌቶች ኢትዮጵያን ከፍ በማድረግ የጥነት አባቶች ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ተምሳሌት ያደረጉበትን የአሸናፊነት ታሪክ" ደግመዋል ብለዋል።
በተለይም አዲሱ ትውልድ በመደጋገፍና በመተባበር ታሪክ መስራት እንደሚቻል ከአትሌቶቻችን ልምድ በመውሰድ አንድነቱን ማጠናከር እንዳለበት ነው የገለጹት
"አትሌቶቻችን ኢትዮጵያን በማድመቅ ታሪካዊ ድል በማስመዝገባቸው ምሥጋና ሊቸራቸው ይገባል" ያሉት ደግሞ የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ አቶ ሙሉጌታ ቢራቱ ናቸው።
ድሉ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መስኮች ጭምር መሆን እንዳለበት ገልጸው፣ ሀገራዊ የብልፅግና ጉዞን ለማሳከት አንድነትን ማጠንከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።