ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሌም የሰራዊቱ ደጀን በመሆኑ የከበረ ምስጋና ይገባዋል--የመከላከያ ሰራዊት አባላት

ሐምሌ 22/2014 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገር ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ በመመከት ሁሌም የሰራዊቱ ደጀን በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል ሲሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተናገሩ፡፡

'ከአጣነው ይልቅ የተሰጠን ይበልጣል' በሚል በትናትናው እለት በአገር አቀፍ ደረጃ የምስጋና መርሓ ግብር ተካሂዷል፡፡

በዚህም የመንግስት ተቋማት እንደየዘርፋቸው ምስጋና ለሚገባቸው ምስጋናን ቸረዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ለሰራዊቱ ደጀን የሆነውን የኢትዮጵያን ሕዝብ አመስግነዋል፡፡

በአገር መከለከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ስነ-ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክቶሬት አባል የሆኑት ሻለቃ አስቻለው ሌንጫ ''የኢትዮጵያን ሕዝብ አመስግኖ ማብቃት አይቻልም'' ይላሉ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በብሔራዊ ክብሩ፣ በሉዓላዊነቱና በነጻነቱ የማይደራደር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ደጀንነቱን ደግሞ ደጋግሞ በተግባር ያሳየና ያስመሰከረ መሆኑንም እንዲሁ።

ኢትዮጵያ የሉዓላዊነት አደጋ በተደቀነባት ጊዜ የውጊያ ቀጣና ድረስ በአካል በመሄድ ይህንኑ ተግባሩን  በተግባር አረጋግጧል፤ ለዚህም ትልቅ ምስጋና ይገባዋል ነው ያሉት።

በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በሻገር የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ወላጆች ምስጋና እንደሚገባቸውም ነው የጠቀሱት፡፡

ልጆቻቸው የአገርን ክብርና ዳር ድንበር እንዲያስከብሩ ትልቅ ውለታ የዋሉ በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል ነው ያሉት።

ሌላኛው የዚሁ ዳይሬክቶሬት አባል የሆኑት ሻለቃ ዴቢሶ ዳፋም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ምስጋና እንደሚገባው ተናግረዋል።

''እኛም ለእሱ ቆማናል፤ እሱም ለእኛ ደግሞ ደጀን ሆነው በአንድነት አገራችንና የአገራችንን ክብር ከፍ እያደረግን ነው'' በማለት ይገልጻሉ።

በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ክፍ ብሎ እንዲውለበለብ ላደረጉት አትሌቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

''ስፖርተኞቻችን የማንነታችን መገለጫዎች ናቸው'' የሚሉት ሻለቃ ዴቢሶ ''የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ እንደማየት የሚያስደስት ነገር የለም'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም