ቀጥታ፡

መጽሐፍት በምክንያት የሚያምን ትውልድ መፍጠሪያ ቁልፍ መሳሪያዎች በመሆናቸው የንባብ ባህላችንን ልናጎለብት ይገባል--አንባቢያን

ሐምሌ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) መጽሐፍት በምክንያት የሚያምን ትውልድ መፍጠሪያ ቁልፍ መሳሪያዎች በመሆናቸው የንባብ ባህላችንን ልናጎለብት ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው አንባቢያን ተናገሩ።

ምክንያታዊ ትውልድ ለመፍጠር ወጣቱ ማህበራዊ ድረ ገፆችን ለዲጅታል መጽሐፍት ማንበቢያ ሊጠቀምባቸው እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ወጣቱ ትውልድ ከአመክንዮ ይልቅ ስሜት ካሸነፈው፣ አካላዊ ብቃቱ ካልጎለመሰና አስተሳሰቡ ካልጎመራ ለአገር መጻዒ እድልና ህልውና አደጋ ነው።

አገርን ለመጭው ትውልድ ማውረስ ሲባልም አገር ተረካቢውን ዜጋ በዕውቀትና ምርምር ኮትኩቶ ማሳደግና ምክንያታዊ ብቁ ዜጋ እንዲሆን ማስቻል ነው።

አቶ ተሾመ በቀለ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃህፍት አገልግሎት ማንበብ ከጀመሩ 30 ድፍን ዓመታትን አስቆጥረዋል።

ወጣት አዛርያስ ኃይለጊዮርጊስ ደግሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃህፍት አገልግሎት ባለሙያ ከመሆኑ ባሻገር ጊዜውን በንባብ የሚያሳልፍ ወጣት ነው።

አቶ ተሾመ እና ወጣት ዘካሪያስ ምክንያታዊነት በጥልቅ ንባብ የሚገኝ ጸጋ በመሆኑ አገር ተረካቢው ወጣት ራሱን በዕውቀት፣ ፈጠራና ምርምር በላቀ ደረጃ አቅሙን ማጎልበት እንዳለበት ይመክራሉ።

በኢትዮጵያ በህትመት ዋጋ ንረት የመጽሐፍት ዋጋ በየጊዜው ቢንርም ምሉዕ ሰው ሆኖ ለመቅረብ ግን  ማንበብ ብቸኛው አማራጭ በመሆኑ በዋጋ ንረት ሊገደብ አይገባም ባይ ናቸው።

የመፅሐፍት ዋጋ ከፋይዳው እና ለሌሎች ጉዳዮች ከምናወጣው ወጭ አንጻር እምብዛም የተጋነነ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

በመሆኑም ወጣቱ ከዕውቀት ከመራቅ መጽሐፍትን በውድ ዋጋ ገዝቶ ማንበብ የተሻለ እንደሆነ አስረድተዋል።

መፅሐፍትን ገዝቶ ማንበብ ባይቻል እንኳን ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት አገልግሎት፣ አብርሆት ቤተ መፃህፍትና ሌሎች ተቋማት  ነፃ የንባብ አገልግሎት የሚገኝባቸው ስፍራዎችን ይጠቅሳሉ።

በኢትዮጵያ መጸሐፍትን የማንበብ ባህል በማህበራዊ ድረ ገፆች የተነጠቀ ይመስላል የሚሉት አስተያየት ሰጭዎቹ፤ ክረምቱን በእረፍት የሚያሳልፉ ተማሪዎችና መምህራን ጊዜያቸውን በማንበብ ማሳለፍ አለባቸው ብለዋል፡፡

ለአብነት መምህራን ከአስር ዓመት በላይ የማይቀየር የማስተማሪያ ሞጁል ላይ ብቻ ተንጠልጥለው ከቀሩ፤ ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው ውጭ ተጓዳኝ መጽሐፍትን ካላነበቡ የፈጠራ አቅማቸውን ማሳደግ አይችሉም ብለዋል፡፡

የሰው ልጅ በማንኛውም ጊዜ ማንበብ እንዳለበት በመግለጽ፤ ክረምቱን በቂ ጊዜ ያላቸው ሰዎች ለበጋ ወቅትም ማንበብያ እንደ መነሻ ጊዜ ሊጠቀሙበት ይችላሉ ብለዋል፡፡

በጋዜጦችና መጽሔቶች ከ10 እስከ 20 ደቂቃ በመጀመር በብዙ ሺህ የሚቆጠር ገፅ ያላቸው ጥራዝ መጽሐፍትን የማንበብ ልምድ ማዳበር ይቻላል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃህፍት አገልግሎት የአብያተ መጽሐፍት ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ተፈራ በኢትዮጵያ የንባብ ባህል ዝቅ ያለ ደረጃ ላይ ቢሆንም መሻሻል እንዳለ ይገልፃሉ፡፡

ነገር ግን  የመገናኛ ብዙሃን የሰጡት ትኩረት፣ የትምህርት ስርዓቱ፣ ወጣቶች በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ ባሉ አጫጭር ፅሁፎች መጠመድ ለንባብ ባህላችን ዝቅ ማለት እንደ ችግር ይወሰዳሉ ብለዋል፡፡

አገልግሎቱ አንባቢ ትውልድ መፍጠርና አንባቢዎችን ማበረታታት የሚያስችሉ፤ የማጣቀሻ፣ የህግ ክምችት፣ የመዛግብት፣ የኢትዮጵያ ጥናትና ሌሎችም  ቤተ መፃህፍት በማዘጋጀት በሳምንት ሰባት ቀናት ለአንባቢያን ክፍት አድርጓል ብለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር ወጣቶችን ለማሳተፍ የንባብ ሳምንት፣ የሥነ ጽሁፍ ምሽትና የመጽሐፍት ግምገማ መድረኮችና ኤግዚቢሽን እናዘጋጃለን ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ አንባቢና ምክንያታዊ ትውልድ ለመፍጠር ወጣቱ ማህበራዊ ድረ ገፆችን ለዲጅታል መጽሐፍት ማንበቢያ እንዲጠቀምባቸው ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የህዝብ ቤተ መፃሕፍትን ማስፋፋት፣ ደራሲያንን ማበረታታት፣ ወጣቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የንባብ ክበብ ማቋቋምና መገናኛ ብዙሃን ትኩረት እንዲሰጡት በማድረግ የማንበብ ልምድን ማዳበር ይቻላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም