የመከላከያ ሰራዊቱ እና አትሌቶች ድል የአገር ፍቅርና የጠንካራ ቡድን ስራ ውጤት ነው- ብርጋዴር ጀኔራል ሁሉአገርሽ ድረስ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሰራዊቱ እና አትሌቶች ድል የአገር ፍቅርና የጠንካራ ቡድን ስራ ውጤት ነው- ብርጋዴር ጀኔራል ሁሉአገርሽ ድረስ
አዲስ አበባ ሐምሌ 22/2014(ኢዜአ) የመከላከያ ሰራዊቱ እና አትሌቶች ድል የአገር ፍቅርና የጠንካራ ቡድን ስራ ውጤት መሆኑን ብርጋዴር ጀኔራል ሁሉአገርሽ ድረስ ተናገሩ፡፡
ከጥንትም ጀምሮ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ስሟ እንዲከበር፣ ዝናዋ እንዲናኝ፣ አሸናፊነት መገለጫነቷ እንዲደምቅ፣ ጀግንነቷ እንዲጎላ ወታደሮቿ በተሰማሩበት ዓለምአቀፍ ግዳጆች ሁሉ አስመስክረዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከጦር ሜዳው ወኔና ጀብዱ ባሻገር በስፖርት ዓለምን ያስደመሙ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ያውለበለቡ ብርቅዬ ልጆቿም ያፈራ ተቋም ነው።
ጦር ሠራዊት፣ ምድር ጦር በኋላም ከ1948 ጀምሮ እስከ 1980ዎቹ መጀመሪያ "መቻል" በሚለው ዝነኛ ስሙ በሚታወቀው ስፖርት ክለቡ ውስጥ መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ክብር ያጎሉ አትሌቶቹን አፍርቷል።
በባዶ እግሩ የሮጠና የኦሎምፒክ ባለድሉ ሻምበል አበበ ቢቄላ፣ ማርሽ ቀያሪው ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር፣ ሻምበል ማሞ ወልዴና መሰሎቹ ከቀድሞዎቹ የሰራዊቱ ስመ-ጥር አትሌቶች ይጠቀሳሉ።
ተቋሙ በየወቅቱ የረዥም ርቀት ሪከርድ ሰባሪ የሆኑት እንደ አልማዝ አያና፣ ቲኪ ገላና፣ ሙክታር እድሪስ፣ ሙሉጌታ ወንድሙ፣ ኢማና መርጊያ፣ ሱሌ ዑቱራና መሰሎቹን ለአገር ያበረከተና አሻራውን ያሳረፈ የምርጥ ስፖርተኞች መፍለቂያ ማዕከል ነው።
በቅርቡ ወደ ቀድሞ 'መቻል ስፖርት ክለብ' ስያሜው የተመለሰው የሰራዊቱ ስፖርት ክለብ በ18ኛው ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ሻምፒዮናም ሁለት አትሌቶቹ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ለአገራቸው አምጥተዋል።
በመከላከያ የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ብርጋዴል ጄኔራል ሁሉአገርሽ ድረስ ከድሮ ጀምሮ ሰራዊቱ በተሰለፈበት ዓውደ ግንባር ሁሉ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ማውለብለብ ነባር መገለጫው እንደሆነ ገልፀዋል።
የመከላከያ ሰራዊት በድልና አሸናፊነት ሰንደቋን ከፍ የሚያደርገው በቡድን ስራ እንደሆነ ገልጸው፤ ከሰሞኑ የተገኘው የአትሌቶች ድልም የቡድን ስራ ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል።
ሰራዊቱና አትሌቶች የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ በማውለብለብ እንደሚያመሳስላቸው፣ በዓላማ ደረጃም ስፖርትም ለሰላም፣ ሰራዊቱም ለሰላም ማስከበር መሰለፉ አንድ እንደሚያደርጋቸው ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያዊያን በፈተናዎች ውስጥም ሆነን በተደራጀና በተቀናጀ በፍቅር ከሰራን ድልን ማጣጣም እንደሚቻል በአትሌቶች አይተናል ብለዋል።
ሰራዊቱ በግንባር አገሩን እየጠበቀ፣ አትሌቶቹም በዓለም መድረክ ለኢትዮጵያን ከፍታ ተዋድቀዋል ነው ያሉት።
ሴቶች በዐውደ ግንባር እንዳላቸው ጀብዱ ሁሉ ፈታኙን ውጣውረድ ተቋቁምው ለአገራችው ኩራትና ዘብ የሆነ ትግላቸውን አጠናክረዋልም ብለዋል።
በመከላከያ ስነ ልቦና ግንባታ ዳይሬክቶሬት የስፖርት ክፍል ተወካይ ዳይሬክተር ኮሎኔል አብዲሳ ታደሰ እና በመከላከያ አትሌቲክስ የረዥም ርቀት ክፍል መሪ ሻለቃ አማረ አራጌ ስፖርትና ሰራዊት ቁርኝትን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሲሉ ይገልጹታል።
ሰራዊቱ በተለያዩ አየር ንብረትና መልክዓ ምድር ግዳጁን ለመወጣት አካላዊ ብቃቱን የገነባ ሲሆን ይህ ሰራዊትም ለምርጥ ስፖርተኞች መፍለቂያ እንዲሆን አድርጎታል ይላሉ።
በቀጣይም ይህን ተሞከሮ በመያዝ አገርን ሊያኮሩ የሚችሉ አትሌቶችን ለማፍራት እየተጋ መሆኑን ገልጸው፤ በቅርቡ በተደረገው የኦሪገን ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ሻምፒዮናም ሁለት ሜዳሊያ ማምጣታቸውን አስታውሰዋል።
የተገኘው ውጤት የህዝብ አንድነት ካለ የማንወጣው ችግር እንደሌለ ማሳያ እንደሆነ ገልጸው፤ ማንም ዜጋ በተሰማራበት ግዳጅ ከተሰማራ ጀግና ነው ብለዋል።
ህዝባዊ ወገንተኝነት ያለው መከላከያ ሰራዊት ለኢትዮጵያ ሕልውና ብሎም ለዓለም ሰላም ማስከበር እንደሚተጋው ሁሉ በስፖርቱ ዘርፍም የኢትዮጵያን ስም ከፍ ለማድረግ በሪፎርም ላይ መሆኑን ተናግረዋል።