ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለውሃ ሀብት ልማቱ የጎላ አስተዋጽኦ አለው---ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ

ጎንደር ሐምሌ 22/2014  (ኢዜአ) በሀገር ደረጃ ትኩረት የተሰጠው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለውሃ ሀብት ልማቱ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ተናገሩ፡፡

በሚኒስትሩ የተመራ የልኡካን ቡድን በጎንደር ከተማ "ገንፎ ቁጭ" በሚባለው ስፍራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዛሬ አካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በከተሞች የሚታየውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በማሻሻል ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ አለው።

"መርሃ ግብሩ የአካባቢን የአየር ንብረት ሚዛን ከማስጠበቅ በሻገር የመሬት መሸርሸርና ወደ ወንዞች የሚገባውን ከፍተኛ ደለል አፈር በማስቀረት ተፋሰሶችን ለማልማትና ለመጠበቅ እገዛው የላቀ ነው" ብለዋል።

በተለይ በዓባይ ተፋሰስ የሚታየውን የደን መራቆትና የአካባቢ መጎሳቀል ወደቀደመ ልምላሜ በመመለስ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከደለል ስጋት ለመታደግ ዘላቂ መፍትሄ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እውን መሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ መርሃ ግብሩ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በከተማው በአረንዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከሉ ችግኞች 80 በመቶ ያህሉ መጽደቃቸውን የተናገሩት ደግሞ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ናቸው።

ጎንደር ከተማ ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ እጥረት ካለባቸው ከተሞች አንዱ መሆኑን ጠቁመው፣ ውሃ ለማግኘት ችግኞችን ተክሎ በየጊዜው መከባከብ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በሚኒስቴሩ የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ስሜ በበኩላቸው፣ የችግኝ ተከላ መርሀ ግበሩ አረንገዴ አሻራን ከማሳረፍ ባለፈ ከጎንደር ህዝብ ጋር አብሮነትን ለማጠናከር ታልሞ መካሄዱን ተናግረዋል።

በጎንደር ከተማ "ገንፎ ቁጭ" በተባለ ስፍራ ዛሬ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም የሚኒስቴሩ ሠራተኞች እና አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም