አትሌቶቻችን ያስመዘገቡት ድል ኢትዮጵያዊያን ፈተናዎችን በጋራ በመጋፈጥ ለተጨማሪ ድል መትጋት እንዳለባቸው ያመላከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አትሌቶቻችን ያስመዘገቡት ድል ኢትዮጵያዊያን ፈተናዎችን በጋራ በመጋፈጥ ለተጨማሪ ድል መትጋት እንዳለባቸው ያመላከተ ነው
ሐምሌ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) አትሌቶቻችን ያስመዘገቡት ድል ኢትዮጵያዊያን ፈተናዎችን በጋራ በመጋፈጥ ለተጨማሪ ድል መትጋት እንዳለባቸው ያመላከተ መሆኑን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራርና ሠራተኞች "ኢትዮጵያ ታመሥግን" መርሃ-ግብር አከናውነዋል፡፡
በመርሃ-ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ድሉ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ በደማቁ የጻፈና ከፍ ያደረገ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እንደማትፈርስ በተግባር ያረጋገጡ ጀግኖች እንዳሉ ሁሉ፤ አትሌቶቻችንም የኢትዮጵያን ክብር ዳግም ከፍ አድርገዋል ነው ያሉት፡፡
የተመዘገበው ድልም ሁሉም በተሰማራበት መስክ በትብብር ከሰራ ለድል እንደሚበቃ ትምህርት የሰጠ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ፈተናዎችን በጋራ በመጋፈጥ እና አንዱ ለሌላው እውቅና እና ክብር በመስጠት ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ አሸናፊ እንድትሆን በመደጋገፍና በመተባበር መሥራት እንደሚገባም እንዲሁ፡፡
ድሉ ኢትዮጵያ ችግሮቿን እያሸነፈች በመጣችበት ወቅት ላይ የተመዘገበ መሆኑ ደግሞ ልዩ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በተለይ የታላቁ የሕዳሴ ግድብና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች በስኬት እየተከናወኑ ባሉበት በዚህ ወቅት የተመዘገበው ድል ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያንን ያኮራ መሆኑን ነው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት፡፡
በአሜሪካ ኦሪገን ከተማ በተከናወነው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ለአንድ ዓላማ በትብብር በመሥራት ለአገራቸው አሥር ሜዳሊያዎችን ማምጣት የቻሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም በውድድሩ ከአሜሪካ ቀጥላ በዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡