የሩጫችን መዳረሻ የበለጸገች ሃገር መፍጠር በመሆኑ ለኢትዮጵያ ከፍታ መስራት ይጠበቅብናል- አቶ ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
የሩጫችን መዳረሻ የበለጸገች ሃገር መፍጠር በመሆኑ ለኢትዮጵያ ከፍታ መስራት ይጠበቅብናል- አቶ ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ ሃምሌ 21/2014 (ኢዜአ) የሩጫችን መዳረሻ የበለጸገች ሃገር መፍጠር በመሆኑ ለኢትዮጵያ ከፍታ ተግተን መስራት ይጠበቅናል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስገነዘቡ፡፡
"የኢትዮጵያ ታመስግን" መርሃ ግብር በሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት አዳራሽ ዛሬ ተካሂዷል፡፡
ዛሬም እንደትናንቱ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን፣ እጃችንን ለምስጋና እንዘረጋለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉትን መልእክት ተከትሎ የሲዳማ ክልል አትሌቶችን በማመስገን ቀኑን አስቧል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ባስተላለፉት መልእክት "ድሉ በፈታኝ ወቅት የተገኘ አትሌቶች ለመላው ኢትዮጵያዊያን ያበረከቱት የክብር ስጦታ ነው" ብለዋል፡፡
አትሌቶቹ በግልና በጋራ ያደረጉት ጠንካራ ዝግጅትና በውድድሩ ጊዜ ያሳዩት ከራስ በላይ ለሃገር ጥቅምና ክብር መስራታቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡
ሃገራት ከድህነት ወደ ልእልና የሚያደርጉት ጉዞ በሩጫና በትግል የታጀበ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ "ሁላችንም በውድድር ውስጥ መሆናችንን ተገንዝበን ልንሰራ ይገባል" ብለዋል፡፡
"አሁንም በፈተና ውስጥ በመሆናችን ፈተናውን ለማለፍ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልገናል" ሲሉም አክለዋል።
"የሩጫችን መዳረሻ የበለጸገች ሃገር መፍጠር በመሆኑ ለኢትዮጵያ ከፍታ ተግተን መስራት ይጠበቅብናል፣ ይህንንም ከአትሌቶች መማር ይኖርብናል" ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
በፈተናዎች ውስጥ አንጻባራቂ ድሎች እየተመዘገቡ መሆኑን የጠቆሙት ርእሰ መስተዳደሩ ሃገር ለመበታተን የተጠነሰሰውን የጠላት ሴራ ተቋቁመን ሽንፈትን በድል የለወጥንበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
"ከውድቀት ወደ ድል፣ ተስፋ ከመቁረጥ ወደ ከፍታ መሻገር ስለሚገኝ ማማረር ሳይሆን ማመስገን፣ መከፋት ሳይሆን መደሰት በመልመድ የሚታየውን ብሩህ ተስፋ ማስቀጠል ይገባል" ብለዋል፡፡
ከአትሌቶቹ ድል ውጤት በፊት ዳገት መውጣትና መውረድ መኖሩን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ሁሉም በተሰማራበት መስክ ተግቶ በመስራት የኢትዮጵያን ከፍታ ማረጋገጥ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ድሉ በአስከፊ ጊዜ የተገኘና የኢትዮጵያዊያንን አይበገሬነት ያሳየ፣ ወንድማማችነትን ያጠናከረ በመሆኑ በክልሉ ህዝብና መንግስት ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል ፡፡
በሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ቅጥር ግቢ በተካሄደው "የኢትዮጵያ ታመስግን" መርሃ ግብር ላይ የክልሉ ካቢኔ አባላትና የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡