አንድ ሆነን ከሠራን የማንሻገረው ፈተና እንደሌለ አትሌቶቻችን አሳይተውናል - አቶ አሻድሊ ሃሰን - ኢዜአ አማርኛ
አንድ ሆነን ከሠራን የማንሻገረው ፈተና እንደሌለ አትሌቶቻችን አሳይተውናል - አቶ አሻድሊ ሃሰን
አሶሳ ፤ ሐምሌ 21 / 2014 (ኢዜአ ) ፡- ኢትዮያውያን አንድ ሆነን ከቆምን የማንሻገረው ፈተና እንደሌለ በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደማቅ ታሪክ ያስመዘገቡ አትሌቶቻችን አሳይተውናል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሃሰን ገለጹ፡፡
አኩሪ ድል ላስመዘገቡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን አባላት “አንድ ሆነን እንስራ ፤ ኢትዮጵያ ታሸንፍ” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአሶሳ የምስጋና ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት ኢትዮጵያ ፈተናዎቿን እየተሻገረች ወደ ብልጽግና መድረሷ አይቀሬ እየሆነ መጥቷል፡፡
18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደማቅ ታሪክ ያስመዘገቡ አትሌቶቻችን ኢትዮጵያውያን አንድ ከሆንን የማንሻገረው ፈተና እንደሌለ በተግባር አረጋግጠውልናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አትሌቶቹ ታላቅ ክብር ይገባቸዋል ብለዋል አቶ አሻድሊ፡፡
በፈተናው ውስጥ ሆነን ላገኘነው ውጤት ፈጣሪን ማመስገን እንደሚያስፈልግና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ጸሐይ ሞርካ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያን የገጠማቸውን እልህ አስጨራሽ ጉዞ እያለፉ ወደ ድል እየሄዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የክልሉ ፖሊስ ማርች ባንድ ሀገራዊ ዜማዎችን ያቀረበ ሲሆን ተሳታፊዎቹ ለአትሌቶች ያላቸውን ክብር እጃቸውን በልባቸው ላይ ጭነው ሠንደቅ ዓላማ በማውለብለብ አሳይተዋል፡፡
በዝግጅቱ በአሶሳ ከተማ የሚገኙ መንግስታዊ ተቋማት አመራሮች እና ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡