ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት በማስጠበቅ የጋራ ትብብርና ጥረታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል- ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት በማስጠበቅ የጋራ ትብብርና ጥረታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል- ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
ሐምሌ 21/2014 (ኢዜአ) ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት በማስጠበቅ የጋራ ትብብርና ጥረታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ተናገሩ።
የኮሚሽኑ አመራርና ሠራተኞች የ"ኢትዮጵያ ታመሥግን" መርሃ ግብር አካሂደዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል፤ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት በዓለም መድረክ አሸናፊ በመሆን ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ለታላቅ ክብር ላበቁን አትሌቶች ምስጋናና ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።
የድሉ ዋነኛ መሰረት የትብብርና አንድነት ውጤት መሆኑን ጠቅሰው በሁሉም መስክ ኢትዮጵያን አሸናፊ ለማድረግ ሁላችንም በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።
በኦሪገን የዓለም ሻምፒዮና አትሌቶቻችን ያስመዘገቡት ድል ተባብሮ በመሥራት ውጤት ማምጣት እንደሚያስችል ያየንበት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስም ለኢትዮጵያ ክብርና ዘላቂ ሰላም ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በመተባበር በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያን ለማፍረስ የውስጥ ባንዳዎች ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር የሚያደርጉትን የጥፋት እንቅስቃሴ በማክሸፍ ድል እያስመዘገብን እንገኛለን ብለዋል።
ለድልና አሸናፊነት የጋራ ጥረት ወሳኝ በመሆኑ የሽብር ቡድኖችን በተባበረ ክንድ ለማሸነፍ እንሰራለን ያሉት ኮሚሽነር ጀነራሉ የኢትዮጵያን ጠላቶች በመደምሰስ ዘላቂ ሰላሟን እናስቀጥላለን ነው ያሉት።
ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት በማስጠበቅ የጋራ ትብብርና ጥረታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ከተገኙት የፖሊስ አባላት መካከል ምክትል ኮማንደር ፀደይ ሙልሳ እና ዋና ሳጅን መሐመድ ሰይድ፤ በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቶች ባስመዘገቡት ድል መኩራታቸውን ገልጸዋል።
እኛም ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት መከበር አስፈላጊውን ሁሉ መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።