ምክር ቤቱ ኢትዮጵያን ከፍ ላደረገው የአትሌቲክስ ቡድን ምስጋናውን አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ ኢትዮጵያን ከፍ ላደረገው የአትሌቲክስ ቡድን ምስጋናውን አቀረበ
ባህር ዳር (ኢዜአ) ሐምሌ 21/2014 የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በዓለም አቀፍ መድረክ ላስመዘገበው ድል የአማራ ክልል ምክር ቤት አመሰገነ።
የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈንቱ ተስፋዬ እንዳሉት አትሌቶቻችን ያስመዘገቡት ድል መላው የኢትዮጵያን ህዝብ ያኮራ ነው።
የተገኘው ድል በዓለም መድርክ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ከማድረግ ባለፈ በችግር ውስጥ ሆኖም ማሽነፍ እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ገልፀዋል።
"ድሉም ከተባበርንና ከተጋገዝን የገጠሙንን ችግሮች በመሻገር ተጨማሪ ድሎችን ማስመዝገብ እንደምንችል ትምህርት የሰጠ ነው" ብለዋል።
"አንድ ሆነን እንስራ - ኢትዮጵያ ታሽንፍ" በሚል መሪ ሃሳብ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ላደመቁ ጀግኖች አትሌቶች የምክር ቤቱ አባላት የአንድ ደቂቃ የምስጋና ስነ ስርዓት አቅርበዋል።
በተጨማሪም የምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር በመዘመር ለሀገር ባለውለታዎች አመስግነዋል።
በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከዓለም 2ኛ ከአፍሪካ 1ኛ በመውጣት ደማቅ ታሪክ ለጻፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልኡካን ቡድን ዛሬ ደማቅ አቀባበል መደረጉ የሚታወስ ነው።
ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የክልሉን የ2015 በጀት ዓመት ከማጽደቅ በላይ የንጋት ቦርድ አባላትን፣ የዳኞችና ሌሎች ሹመቶችን አጽድቋል።