ድሉ እኛ ኢትዮጵያውያን ከተጋገዝን ሀገራችንን ማሻገር እንደምንችል ያሳየ ነው- የሐረር ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ድሉ እኛ ኢትዮጵያውያን ከተጋገዝን ሀገራችንን ማሻገር እንደምንችል ያሳየ ነው- የሐረር ነዋሪዎች
ሐረር፤ ሐምሌ 21/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አትሌቶች በአለም መድረክ ያስመዘገቡት ድል እኛ ኢትዮጵያውያን ከተጋገዝንና ከተደጋገፍን ሀገራችንን ማሻገር እንደምንችል ያሳየ መሆኑን የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
“አንድ ሆነን እንስራ ኢትዮዽያ ታሸንፍ” በሚል መሪ ሀሳብ የመንግስት ሰራተኞች፣ የጸጥታ ሃይሎችና ሌሎችም የከተማዋ ነዋሪዎች የተሳተፉበት ለጀግኖች አትሌቶች የምስጋና መርሃግብር ተካሂዷል ፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች ጀግኖች አትሌቶች በአለም መድረክ የኢትዮጵያን ስም በማስጠራታቸው የተሰማቸውን ደስታ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፤ ምስጋናም አቅርበዋል።
ከመረሃ ግብሩ ተሳታፊዎች ፋሚ ሙክታር ፤ አትሌቶቹ ባስመዘገቡት አኩሪ ድል መደሰቱን ገልጾ፤ ድሉ እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ከሰራን ኢትዮጵያን ማሻገር እንደምንችል ያሳየ ነው ብሏል፡፡
አቶ ፈጠነ በጅጋየው በበኩላቸው፤ በአለም መድረክ ላይ አንድ በመሆን ጀግኖች የኢትዮጵያ አትሌቶች ያስመዘገቡት አኩሪ ድል ሀገሪቱን ከማንኛውም ችግር ማውጣት እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል።
በአለም መድረክ በአንድንት እና በመተባበር ያስመዘገብነውን ድል ድህንትን በመዋጋት እና ችግሮቻችንን በጋራ የማለፍ አቅም እንዳለን የሚያሳይ ነው ብለዋል ፡፡
ጀግኖች አትሌቶቻችን በአንድነት ሆነው ሀገርን በማስቀደም በአለም መድረክ ላይ ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርገዋል ያለው ደግሞ ወጣት ከሊፋ መሀመድ ነው።
በዚህም ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፤ አንድነትን ከአትሌቶቻችን ተምረን በልማት እና ሰላም አንድነታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብሏል።
በመረሃ ግብሩ ላይ የሐረሪ ክልል የመንግስት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ህኖክ ሙሉነህ ባስተላለፉት መልዕክት፤ እኛ ኢትዮዽያዊያን በችግር ውስጥ ሆነን ማሸነፍ እናውቅበታለን ብለዋል።
በአለም መድረክ የሀገራችን ስም ከፍ ብሎ እንዲጠራ ላደረጉ ጀግኖች አትሌቶች በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና አቀርባለሁ ያሉት ሀላፊው፤ የክልሉ ህዝብ በአካባቢው እየተከናወኑ በሚገኙ የሰላምና ልማት ስራዎች ላይ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል ።
የምስጋና መርሃ ግብሩ በተመሳሳይ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም የመንግስትና የግል ተቋማት መካሄዱን የኢዜአ ሪፖርተር ከሐረር ዘግቧል።