ቀጥታ፡

በዓለም አደባባይ የአትሌቶቻችን አሸናፊነት ከድልም በላይ በትብብርና አንድነት አገራዊ ፍቅራቸውን ያሳዩበት ነው

ሐምሌ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዓለም አደባባይ የአትሌቶቻችን አሸናፊነት ከድልም በላይ በትብብርና አንድነት አገራዊ ፍቅራቸውን ያሳዩበት ነው ሲሉ በአትሌቶች የአቀባበል መርሃ ግብር ላይ የተገኙ ታዳሚዎች ተናገሩ።

በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በድል አድራጊነት ለተመለሰው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልኡካን ቡድን በአዲስ አበባ ደማቅ አቀባበል ተደርጓል።

የልዑካን ቡድኑን በማርች ባንድ ጭምር በማጀብ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የስፖርት ቤተሰቦችና ሌሎችም ተገኝተው አቀባበልና ምስጋና አቅርበዋል።

የልኡካን ቡድኑ በማለዳ ከቦሌ ከስካይላይት ሆቴል በመነሳት በመስቀል አደባባይ እስጢፋኖስ፣ በ4 ኪሎ፣ ፒያሳ፣ ቸርችል ጎዳና በመዘዋወር ደስታቸውን ለህዝቡ አጋርተዋል።

በሜክሲኮ አደባባይ በመዞር ወደ መስቀል አደባባይ በማቅናትም "የእንኳን ደህና መጣችሁ" አቀባበል በማድረግ ምስጋና ቀርቦላቸዋል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ከታደሙት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ታዳሚዎች እንደገለጹት በዓለም አደባባይ የአትሌቶቻችን አሸናፊነት ከድልም በላይ በትብብርና አንድነት አገራዊ ፍቅራቸውን ያሳዩበት ነው።

ከዓለም አገሮች ጋር ተወዳድሮ በአትሌቲክስ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ከድልም በላይ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም አትሌቶቻችን ባስመዘገቡት ድል ለአገራችን ኩራት ሲሆን ለዜጎቿ ታላቅ የደስታ ቀን ሆኗል ብለዋል።

በአሜሪካ ኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከተገኘው ድል በላይ አትሌቶቻችን የኢትዮጵያዊያንን መተሳሰብና ፍቅር በተግባር አሳይተውናል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው አራት የወርቅ፣ አራት የብርና ሁለት የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ታሪካዊ ድል ማስመዝገቧ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም