መከራና ፈተና ቢበዛም ፅናትና ቁርጠኝነት ካለ ስኬትና ድል እንዳለ አትሌቶች አሳይተዋል - ዶክተር አብርሃም በላይ - ኢዜአ አማርኛ
መከራና ፈተና ቢበዛም ፅናትና ቁርጠኝነት ካለ ስኬትና ድል እንዳለ አትሌቶች አሳይተዋል - ዶክተር አብርሃም በላይ

ሐምሌ 21/2014 (ኢዜአ) መከራና ፈተና ቢበዛም ፅናትና ቁርጠኝነት ካለ ስኬትና ድል እንዳለ አትሌቶች አሳይተዋል ሲሉ የአገር መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት የመቻል ስፖርት ቡድን በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ የምስጋና ስነ ስርዓት ተካሂዷል።
የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰና ሌሎች ጀኔራል መኮንኖች እና የስፖርት ቤተሰቦች በተገኙበት የምስጋና ስነ ስርዓቱ የተካሄደው።
በ18ኛው አለም አቀፍ አትሌቲክስ ሻምፒዮና መቻል ስፖርት ክለብ አንድ አሰልጣኝና 4 ተወዳዳሪዎች አሳትፏል።
የመቻል አትሌቶች አንድ የብር ሜዳሊያ በመሰረታዊ ወታደር የወርቅውሃ ጌታቸው፣ አንድ የነሀስ ሜዳሊያ በሀምሳ አለቃ ዳዊት ስዩም ለአገራቸው አስገኝተዋል።
ኢትዮጵያ ለዚህ ክብር እንድትበቃ ያደረጉ አትሌቶች ሕብረ ብሔራዊነትን ከአንድነት ጋር አጣምረው አንድነት ለድል እንደሚያበቃ በዓለም መድረክ አሳይተዋል ብለዋል።
በአንድነት በጋራ ስንራመድ ድሎቻችን ደማቅና አኩሪ ይሆናሉ፤ አገርን አስቀድመን ለሰንደቅ ዓላማ ከቆምን ከተዋደቅን ክብር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ አትሌቶች በኦሪገን የዓለም ሻምፒዮና ያሳዩት አሸናፊነት መከራና ፈተና ቢበዛም ፅናትና ቁርጠኝነት ካለ ስኬትና ድል እንዳለ አሳይተውናል ብለዋል
እንደ አገር ፈተናዎች ቢበዙም የአገር መከታ በመሆናችን እንደ አትሌቶቻችን በመከራም ጊዜ እየበረታን ወደ ፊት እንጓዛለን ብለዋል።
በመከራ ፀንተን ወደ ፊት መጓዝ አለብን፤ ለድል ያበቁ የመቻል ስፖርት ክለብ አትሌቶችም ምስጋና ይገባቸዋል በማለት ሚኒስትሩ ተናግረዋል።