ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በፈተናዎች የማትሸነፍ ሀገር መሆኗን በየዘመኑ በማሳየት ህያው ምስክር ናት

ሐምሌ 21/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በፈተናዎች የማትሸነፍ ሀገር መሆኗን በየዘመኑ በማሳየት ህያው ምስክር መሆኗን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ተፈሪ ፍቅሬ ተናገሩ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አመራርና ሠራተኞች የ"ኢትዮጵያ ታመሥግን" መርሃ ግብር አካሂደዋል።

በመርሃ ግብሩ ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በፅናት እንድታልፍ ላደረጋትና በርካታ መልካም ነገሮችን ለቸራት ፈጣሪ ምስጋና አቅርበዋል።

በዚሁ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ተፈሪ ፍቅሬ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ቅኝ ገዥዎችን እምቢ ያለችና ሴራዎችን በመበጣጠስ ሉዓላዊነቷን ያላስደፈረች ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል።

በርካታ ውጣ ውረዶችን በማለፍ አቅም የላቸውም አይገነቡትም የተባለው ታላቁ የህዳሴ ግድብን በኢትዮጵያውያን ጥሪት በመገንባት ኃይል እንዲያመነጭ መደረጉ የአሸናፊነቷ ማሳያ ነው: ይህ እንዲሆን ላበረታን ፈጣሪም ምስጋና ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያን በስፖርቱ መስክ ከጥንት እስከዛሬ ሰንደቅዓላማዋ ከኃያላኑ ተርታ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ላደረጉ አትሌቶቻችንና ለፈጣሪ ምስጋና ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ድሏንና ታሪኳን ማስቀጠል የቻለች ሀገር ናት ያሉት ተፈሪ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያጋጠሙ ፈተናዎችን በህብረ ብሔራዊ አንድነት መሻገር መቻሉን ጠቅሰዋል።

ሀገሪቱ መሪን እስከ ጦር ሜዳ ያስዘመተ የፈተና አውድ ውስጥ እንደነበረች ጠቅሰው መሪዎችና ህዝቡ በመናበብ ሀገራቸውን ከመበታተን ስጋት ማውጣታቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ ላይ ፈተናዎችን ተሻግረን አንፃራዊ የሰላም ተስፋ ማየት ጀምረናል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ፈጣሪ ሊመሠገን ይገባዋል ብለዋል።

መሪና ተመሪ ተግባብተው ለጋራ ዓላማ ከሰሩ ስኬት አይቀሬ መሆኑን አንስተው፥ በቀጣይም በሁሉም የልማት መስኮች በአንድነት መረባረብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ጫናዎች ኢትዮጵያን ለበለጠ ሰላም ለብልፅግና በምታደርገው ጉዞ  ያበረቷታል እንጂ ወደኋላ አይጎትቷትም ብለዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያጋጠሟትን ሴራዎችና ፈተናዎች በመቋቋም ወደፊት በመገስገስ ህያው ምስክር ሆናለች ነው ያሉት።

በዓለም መድረክ የተሠለፉ አትሌቶቻችንም ሀገራቸው ፈተናዎችን በወርቅ በብርና በነሐስ የድል ሜዳሊያዎች ታጅባ እንድታልፍ በማድረጋቸው መመስገን እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም