ምስጋና አንድነትን የማጠናከር ተፈጥሮዊ ሀይል አለው -የጋሞ አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
ምስጋና አንድነትን የማጠናከር ተፈጥሮዊ ሀይል አለው -የጋሞ አባቶች
አርባ ምንጭ ፤ ሐምሌ 21/2014 (ኢዜአ) ምስጋና አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል ተፈጥሮዊ ሀይል ያለው በመሆኑ ባህላችን ልናደርገው ይገባል ሲሉ የጋሞ አባቶች ገለጹ፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው የጋሞ አባቶች፤ የተሻለ የሰራውን የማመስገን ባህል ማድረግ መቻል ተጨማሪ ስንቅና እፎይታ ከመሆን ባለፈ ላልሰራው የአዕምሮ ቁጭት በመፍጠር መልካም የሆነ ፉክክርና መነሳሳትን እንደሚያጎናጽፍ ገልጸዋል።
ከጋሞ አባቶች መካከል አቶ መንግስቱ ደምሴ ፤ ምስጋና የሰው ልጆች ከፈጣሪ ጋር የሚያገናኝ ድልድይ በመሆኑ ከምድራዊነት ባለፈ የነፍስ እርካታን የመስጠት አቅም ስላለው እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ እኛ ኢትዮጵያዊያን በየማህበረሰባችን ባህል ፈጣሪን የምንጠራ፣ ለመልካምና ለበጎ ስራ ከፍተኛ ቦታ የምንሰጥና የስኬት አንዱ ማሳያ አድርገን የምንወስድ ህዝቦች ነን፤ በመሆኑም በህይወታችን አንዱ አካል የሆነው ምስጋና ወሳኝነት እንዳለው ነው ያነሱት ፡፡
በዘመን መለወጫ ጊዜም ዓመቱን ሙሉ በሰላምና በበረከት የጠበቀንን ፈጣሪ በማመስገን አሮጌውን ዓመት የምንሸኝበት የጋራ መገለጫ አለን ብለዋል፡፡
አገልግሎት በየትኛውም ደረጃና በተሰጣቸው ዕድል ለሰጡን አካላት ምስጋና ማቅረብ አንድነትን ከማጠናከርም በላይ የስራ ተነሳሽነትን እንደሚጨምር ገልጸዋል፡፡
በጋሞ ባህል ለሰው ልጆች ካለው ከበሬታ የተነሳ አባቶች ከበቅሏቸው ወርደው ነው ሰላም የሚሉት ያሉት አቶ መንግስቱ ፤ ይህም ያላቸውን ማህበራዊ መስተጋብር ይበልጥ እንዲጠናከር እንደሚመሰጋገኑ አንስተዋል፡፡
ማማረር መጥፎ ጎንና ጉድለትን ብቻ ከመፈለግ የሚመነጭ በመሆኑ ችግርን ከመፍታት ይልቅ የሚያባብስ አደገኛ ባህርይ ነው፤ በመሆኑ እርስ በርስ መመሰጋገን ባህላችን ልናደርገው ይገባል ሲሉ መክረዋል፡፡
በተለይም በማህበራዊ የትስስር ገጾች ፀብ የሚያጭሩ መልዕክቶችን የሚያሰራጩ አካላት ከህሊናቸውና ከፈጣሪያቸው የተጣሉ ናቸው ያሉት ደግሞ ሌላው የጋሞ አባት አቶ ተፈራ ኦይቻ ናቸው፡፡
ፈጣሪን ብናመሰግን እንዲሁም የሚሰሩትንና የሚሞክሩትን በማመስገን ብናበረታታቸው በሀገራችን ያሉ ያልተገለጡ ሀብቶችን ጥቅም ላይ በማዋል በዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ ልንሆን እንችላለን ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህን ጊዜ የምስጋና መልዕክት ማስተላለፋቸው ከአንድ ኢትዮጵያዊ ከሆነ አስተዋይ መሪ የሚጠበቅ በመሆኑ እርሳቸውም ሊመሰገኑና እንዲበረቱ ከጎናቸው ልንሆን ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላለፈዋል፡፡
" ዛሬም እንደ ትናንቱ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን፣ እጃችንን ለምስጋና እንዘረጋለን!! ለአንድ ደቂቃ በያለንበት ቆመን ለኢትዮጵያ አምላክ ምስጋና እንድናቀርብ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሐምሌ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ማስታወቃቸው ይታወሳል።