መከራና ፈተና ቢበዛም ፅናትና ቁርጠኝነት ካለ ስኬትና ድል እንዳለ አትሌቶች አሳይተዋል - ዶክተር አብርሃም በላይ

ሐምሌ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) መከራና ፈተና ቢበዛም ፅናትና ቁርጠኝነት ካለ ስኬትና ድል እንዳለ አትሌቶች አሳይተዋል ሲሉ የአገር መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት የመቻል ስፖርት ቡድን በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ የጀግና አቀባበልና ምስጋና ስነ ስርዓት ተካሂዷል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሐም በላይ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰና ሌሎች ጀኔራል መኮንኖች እና የስፖርት ክለቡ አባላት በተገኙበት ነው የምስጋና ስነ ስርዓቱ የተካሄደው።

በ18ኛው አለምአቀፍ አትሌቲክስ ሻምፒዮና መቻል ስፖርት ክለብ አንድ አሰልጣኝና 4 ተወዳዳሪ አሳትፏል።

ከነዚህም መካከል የመቻል አትሌቶች አንድ የብር ሜዳሊያ በመሰረታዊ ወታደር የወርቅውሃ ጌታቸው፣ አንድ የነሀስ ሜዳሊያ በሀምሳ አለቃ ዳዊት ስዩም ለአገራቸው አስገኝተዋል።

ዶክተር አብርሃም በላይ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለዚህ ክብር እንድትበቃ ያደረጉ አትሌቶች ከፈጣሪ በታች ምስጋና ይገባቸዋል።

ለሰንደቅዓላማ መዋደቅ የመከላከያ ሰራዊት መገለጫ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ እንደ አገር መከራና ፈተና ቢበዛም ፅናትና ቁርጠኝነት ካለ ስኬትና ድል እንዳለ አትሌቶች አሳይተዋል ብለዋል።

በመከራ ፀንተን ወደፊት መጓዝ አለብን፣ ለድል ያበቁ የመቻል ስፖርት ክለብ አትሌቶች ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም