በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ውጤት በጋራ ከተሰራ አሸናፊ መሆን እንደሚቻል ያሳየ ነው - ቀጀላ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ውጤት በጋራ ከተሰራ አሸናፊ መሆን እንደሚቻል ያሳየ ነው - ቀጀላ መርዳሳ
ሀምሌ 21/2014 /ኢዜአ/ በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው አኩሪ ድል በጋራ መስራት ከተቻለ ውጤት ማምጣትና አሸናፊ መሆን እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ተናገሩ ።
በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ10 ሜዳሊያዎች ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በድል ለተመለሰው የአትሌቲክስ ቡድንም ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ በተገኙበት በብሄራዊ ቤተ መንግስት አቀባበልና ሽልማት ተበርክቷል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ፤ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው አኩሪ ድል በጋራ መስራት ከተቻለ ውጤት ማምጣትና አሸናፊ መሆን እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ አትሌቶች ለአገራቸው ድል በጋራ በመስራት የላቀ ድል ማስመዝገባቸውን ጠቅሰው ላደረጉት ሁሉ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።
የአትሌቶቹ ድል ከውጤትም በላይ የኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የጥንካሬያችን መገለጫ መሆኑን በአደባባይ ለዓለም ያሳዩበት አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
የተገኘው ድልም እንደ ሀገር በጋራ ከተሰራ ውጤታማ ከመሆን የሚያግድ አንዳችም ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው ብለዋል።
ጠንካራ አንድነትና ትብብር ካለ በሌሎችም የስራ መስኮች ሁሉ አሸናፊና ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አሳይተውናል ነው ያሉት።
በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና የመጣው ውጤት ሁሉንም ያስደሰተ እና አገር ያኮራ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ለቀጣይ ውጤቶችም የሁሉም ትብብርና የጋራ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው አራት የወርቅ፣ አራት የብርና ሁለት የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ታሪካዊ ድል ማስመዝገቧ ይታወቃል።