ቀጥታ፡

በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተገኘው ውጤት የሁላችንንም ልብ በሃሴት የሞላ እና የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ የሚያስቀጥል ነው- የልዑኩ ቡድን መሪ

ሀምሌ 21/2014/ኢዜአ/ በኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተገኘው ውጤት የሁላችንንም ልብ በሃሴት የሞላ እና የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ የሚያስቀጥል መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ ቡድን መሪ ተናገሩ።

በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ10 ሜዳሊያዎች ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በድል ለተመለሰው የአትሌቲክስ ቡድንም ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ በተገኙበት በብሄራዊ ቤተ መንግስት አቀባበል ተደርጓል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ ቡድን መሪ ተፈራ ሞላ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት  "በዚህ የድል ታሪክ ብስራት ላይ ቆሜ ስናገር ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል" ብለዋል።

ከአትሌቲክስ ቡድኑ ጋር እንቅልፍ አልባ ሆኖ በአብሮነት የቆየውን የኢትዮጵያን ህዝብ እናመሰግናለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሲነሳ  በእነ አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩፅ ይፍጠርና ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ እና ሌሎችም አትሌቶቻችን የተመዘገቡትን ድሎች ለመድገም በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል።

በኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተገኘው ውጤት የሁላችንንም ልብ ሃሴት የሞላ እና የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ የሚያስቀጥል ነው ብለዋል።

የተገኘው  ድል የአትሌቶችና አሰልጣኞች ምልመላ በጥብቅ ዲስፐሊን በመከናወኑ፣ አትሌቶች ቀድመው ወደ ማሰልጠኛ እንዲገቡ በማድረግ በቂ ዝግጅት በመደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በየዕለት ውሎ አፈጻጸምና ግምገማ መደረጉን የጠቀሱት የቡድኑ መሪ፤  ይህም ለተመዘገበው ድል ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

መላው የሀገራችን ህዝብና የመንግስት ድጋፍ ከአትሌቶች ጠንካራ ልፋት ጋር በመደመር ደማቅ የድል ታሪክ መጻፉንም አውስተዋል።

በዚህም ከ192 በላይ ሀገራትጋር ተወዳድረን ከአሜሪካ ቀጥሎ ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ ደግሞ አንደኛ በመሆን ውድድሩን በበላይነት አጠናቀናል ብለዋል።

በአትሌቲክሱ መድረክ የተመዘገበው ውጤትም የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ የሚያስቆም ምንም ሃይል እንደሌለ ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በአራት ወርቅ፣ አራት ብር እና ሁለት ነሃስ የላቀ ድል ማስመዝገቧ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም