የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 27 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 27 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ
ሀምሌ 21/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 27 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀምን በተመለከተ ለሁለት ቀናት የሚያካሂደውን ጠቅላላ ጉባኤ ጀምሯል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ፤ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በ2014 በጀት ዓመት ባንኩ 27 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ገልጸዋል።
የተገኘው ትርፍም ከዕቅዱ 116 ነጥብ 3 በመቶ መሆኑን ጠቅሰው ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ43 ነጥብ 9 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።
የባንኩ አጠቃላይ ኃብት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር መድረሱንም ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።
የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 154 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በማድረስ የዕቅዱን 137 በመቶ ማሳካቱን ገልጸው ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 11 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።
የውጭ ምንዛሬን በማሳደግ ረገድም በበጀት ዓመቱ ከወጪ ንግድ 282 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር፣ ከውጭ ምንዛሪ ግዥ 187 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር፣ ከሐዋላ 2 ነጥብ 2 የሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን ተናግረዋል።
ባንኩ ከሰጣቸው የተለያዩ ብድሮች 120 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሰበሰበ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸርም 102 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ 179 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብድር ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የተሰጠ ሲሆን ከዚህም 34 ቢሊዮን ለግሉ ሴክተር የቀረበ መሆኑን አስታውሰዋል።
በበጀት ዓመቱ የተከፈቱትን 124 አዳዲስ ቅርንጫፎች ጨምሮ አጠቃላይ የቅርንጫፎቹ ብዛት 1 ሺህ 824 መድረሱን ተናግረዋል።
የባንኩ ደምባኞችም 35 ነጥብ 9 ሚሊዮን የደረሱ ሲሆን 5 ሚሊዮኑ ከወለድ አልባ (የሲ ቢ ኢ ኑር) መሆናቸውን ገልጸዋል።
የደምበኞችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ለማሳደግና ግብይትን ከሂሳብ ወደ ሂሳብ እንዲከናወን በማገዝ ከጥሬ ገንዘብ ውጭ ግብይትን ለማስፋፋት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
የተጀመረውን የሪፎርም ስራ በሁሉም የአገልግሎት መስኮች አጠናክሮ ወደ ሙሉ ትግበራ በመግባት የባንኩን ተወዳዳሪነትና ዝግጁነት የማሻሻል ስራ በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል።
በአገልግሎት መስጫ ቦታዎች የሚታየውን የአገልግሎት ጥራት ችግሮች ማረም የተሻለ አገልገሎት ለደምበኞች እንዲቀርብ ይሰራል ብለዋል።
የታዩ አመርቂ ውጤቶችን በማጠናከር በአዲሱ በጀት ዓመት መልካም ተሞክሮዎችን የማሳደግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።