ቀጥታ፡

በአትሌቲክሱ በጋራ ያስመዘገብነው ድል በሌሎችም መስኮች ከተባበርን ማሳካት እንደምንችል ሁነኛ ማሳያ ነው- ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ

ሐምሌ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ)በአትሌቲክሱ በጋራ ያስመዘገብነው ድል በሌሎችም መስኮች ከተባበርን ማሳካት እንደምንችል ሁነኛ ማሳያ ነው ስትል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ገለጸች።

በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በአሥር ሜዳሊያዎች ከዓለም አገራት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በሻምፒዮናው ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አራት የወርቅ፣ አራት የብር እና ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎችን በማሸነፍ በድላቸው አድናቆት ተችሯቸዋል።

የልዑካን ቡድኑን በመምራት በድል የተመለሰችው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፤ "በአትሌቶቻችን አገራችን ኮርታለች" ስትል ተናግራለች።

በውድድሩ የተገኘው ውጤት በሌሎችም መስኮች ከተባበርን ማሳካት እንደምንችል ሁነኛ ማሳያ ነው ብላለች ደራርቱ።

ኢትዮጵያ ሁሌም በጀግኖች ልጆቿ ክብሯ ከፍ ብሎ የሚቀጥል መሆኑንም ተናግራለች።

ኢትዮጵያዊያን በደስታ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በችግር ወቅትም አብሮነታቸውን በማጠናከር አንድነታቸውን እንዲያሳዩም ጥሪ አቅርባለች።

በአሜሪካዋ ግዛት ኦሬገን በተካሄደው የአለም ሻምፒዮና ታሪካዊ ውጤት ያስመዘገበው የአትሌቲክስ ቡድን አዲስ አበባ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም