በኢትዮጵያ ለሰላም ማስፈን ስራዎች ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል- ብሪትኒ ግሌክስነር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ለሰላም ማስፈን ስራዎች ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል- ብሪትኒ ግሌክስነር
ሐምሌ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ)''ኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን ለምታከናውናቸው ተግባራት ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን'' ሲሉ የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ብሪትኒ ግሌክስነር አስታወቁ፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲና በአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ትብብር የተዘጋጀና በሰላም ግንባታ ዙሪያ ያተኮረ የፎቶ አውደ ርዕይ ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ ተከፍቷል፡፡
አውደ ርዕዩን የከፈቱት ብሪትኒ ግሌክስነር ወሎ ዩኒቨርሲቲ ስለ ሰላምና አንድነት የሚሰራቸውን ተግባራት አድንቀዋል፡፡
በተለይ ከጦርነቱ ማግስት የህብረተሰቡን ስነ ልቦና በመጠገንና ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው "በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን ለሚከናወኑ ተግባራት ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል።
ድርጅታቸው ከወሎ ዩኒቨርሲቲው ጋር የጀመረው የሰላም ግንባታ ተግባርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ በበኩላቸው "አሸባሪው ህወሓት የከፈተው ጦርነት በህብረተሰቡ ዘንድ ያደረሰውን የስነ ልቦና ጫና ለማቃለል እየተሰራ ነው" ብለዋል።
በተጨማሪም የመወደሙና የተጎዱ ተቋማትን መልሶ በማቋቋም ለአገልግሎት እንዲበቁ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
"የሚከሰቱ አለመግባባቶች በውይይት፣በባህል እሴቶቻችን እንዲፈቱ በጥናት የታገዘ ስራ እያከናወነ ነው"ያሉት ፕሬዚዳንቱ ሰላም ግንባታ ላይ ልዩ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
በተለይ ከአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ጋር በመቀናጀት ሰላም እንዲሰፍን የሐይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎችና ሀገር ሽማግሌዎችን በማሳተፍ በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
"ህብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ ኢትዮጵያን እንዲያስቀጥል እየተሰራ ነው" ያሉት ደግሞ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የልጅ እያሱ የሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ልማትና ጥናት ተቋም አስተባባሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ተስፋየ ናቸው።
በጦርነቱ ወቅት ተከስተው የነበሩ አስከፊ ሁነቶች፣ከጦርነቱ በኋላ ደግሞ ህብረተሰቡ እንዲረጋጋና ከስነ ልቦና ጉዳት እንዲያገግም የተደረገው ጥረት ውጤታማ እንደነበር ጠቁመው ለውጤቱ የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ድጋፍ አስተዋጾ ማድረጉን አመልክተዋል ።
ከአውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አደም ይመር በሰጡት አስተያየት "ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሰላም ዙሪያ የሚሰራቸው ተግባራት ውጤት እያስመዘገቡ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ብለዋል፡፡
"በጦርነቱ ከደረሰብን የስነ ልቦና ጫና እንድንወጣ ስልጠና ሰጥቶናል" ያሉት አቶ አደም "በየአካባቢያችን ጭምር በግጦሽ፤ በውሃና በሌሎችም የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈታ እያደረገ ነው" ሲሉም አክለዋል፡፡
ለሁለት ቀን በሚቆየው አውደ ርዕይ የጦርነትን አስከፊነትና የሰላምን ጠቀሜታ እንዲሁም የማህበረሰቡን ባህልና እሴቶች የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ለእይታ ቀርበዋል።
በአውደ ርዕዩ የኮምቦልቻ ከተማና የወሎ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤