ቀጥታ፡

በጀግኖች አትሌቶቻችን የተገኘው አኩሪ ድል በየተሰማራንበት መስክ ለመድገም አነሳስቶናል- የድሬዳዋ ነዋሪዎች

ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 20 ቀን 2014(ኢዜአ) ጀግኖች አትሌቶች ተባብረው በአለም አደባባይ ኢትዮጵያን ከፍ ያደረጉበትን አኩሪ ድል በየተሰማሩበት የሥራ መስክ ለመድገም እንዳነሳሳቸው የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በመደመር ስሌት ተባብሮ መንቀሳቀስ ሀገርን የሚያሻግር መሆኑን ከአትሌቶቹ መማራቸውን አመላክተዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የድሬዳዋ ነዋሪዎች፤ ጀግኖቹ አትሌቶች በአለም አደባባይ ያስመዘገቡት አኩሪ ውጤትና ድንቅ ገድል እንዳኮራቸው ገልጸዋል፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ከዲር ሽፋ ፤ ከአትሌቶቻችን ህብረት፣ መዋሃድ፣ መተባበርና መተጋገዝን በመውሰድ ለሀገር ዕድገት፣ ሰላምና ልማት በአንድነት መስራት ይገባል ብለዋል።

የአትሌቶቹ ድል በአለም ደረጃ ከፍታ ላይ ያስቀመጠን ድንቅ የአንድነትና የመተባበር ውጤት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ ዮናስ ስዩም ናቸው።

ለነዚህ አትሌቶች ክብርና ዕውቅና መስጠት በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ መቅረት እንደሌለበትና በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የክብርና የምስጋና ዝግጅት ሊመቻች እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ሌላው የድሬዳዋ ነዋሪ አቶ ዳንኤል ሲሳይ፤ ወጣቱ ከአትሌቶቹ ድል ቆራጥነትና አይበገሬነትን መማር እንዳለበት አመልክተዋል።

ከአሉባልታ ወሬና ከአፍራሽ የማህበራዊ ሚዲያዎች በመራቅ እንደ አትሌቶቹ ሌት ተቀን በመስራት ሀገሩን ከፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም አስተያየት ሰጥተዋል።

በአትሌቲክስ ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት ሁሉም በየተሰማራበት የስፖርትና የስራ መስክ ለመድገም መነቃቃት መፍጠሩን የተናገሩት ደግሞ የድሬዳዋ የቦክስ ክለብ አሰልጣኝ አቶ ኤፍሬም ነጋሽ ናቸው፡፡

በጀግኖች የኢትዮጵያ አትሌቶች አኩሪ ድል እንደተመዘገበው ሁሉ ከነሱ ብርታትና አንድነት በመማር ለሀገር አንድነት፣ ሰላም፣ ፍቅርና ልማት መትጋት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የአትሌቶቹ ድል በየተሰማሩበት የስራ መስክ ሁሉ በጋራና በተናጠል ተባብሮ መስራት የሚያስገኘውን ድንቅ ውጤት ያስተማረ ክስተት መሆኑን ጠቅሰው፤ እነሱም ድሉ በየተሰለፉበት የስራ ዘርፍ ለመድገም እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል፡፡

በመደመር ስሌት ተባብሮ መስራት ሀገርን የሚያሻግር በመሆኑ ከአትሌቶቹ ተምረን ሀገርን ለሚያሻግር ተግባር በቁርጠኝነት መትጋት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም