ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ደምቃ የታየችው በአትሌቶቻችን የጸና አንድነትና የአሸናፊነት ወኔ ነው - የጋሞ አባቶች

አርባ ምንጭ፣ ሐምሌ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዓለም የአትሌትክስ ውድድር ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ደምቃ የታየችው አትሌቶቻችን ባንጸባረቁት የጸና አንድነትና የአሸናፊነት ወኔ ነው ሲሉ የጋሞ አባቶች ተናገሩ።

የጋሞ አባቶቹ ለኢዜአ እንደገለጹት አንድነትን በማጠናከር በሌሎች የልማት ዘርፎችም ውጤት በማስመዝገብ ድሉን ማጠናከር ይገባል።

ከጋሞ አባቶች መካከል አቶ መንግስቱ ደምሴ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት በዓለም አደባባይ ከፍ ብላና ደምቃ በመታየቷ ከፍተኛ ደስታና ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

"ስፖርት ዓለምን ድንበር አልባ ያደረገ እንደመሆኑ መጠን አትሌቶቻችን ዘር፣ ቀለምና ሃይማኖት ሳይገድባቸው ኢትዮጵያን ከፍ ያደረገ ታሪክ የመፃፋቸው ምስጢር አንድነታቸው ነው" ብለዋል።

"አንድ ስንሆን እንጠነክራለን፤ እናሸንፋለን" ያሉት አቶ መንግስቱ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከአትሌቶቻችን ድል ጀርባ ያለውን የአንድነትና የአብሮነት ምስጢር አሻግሮ ማየትና ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የተገኘው ድል የጋራ ውጤት እንጂ በተናጠል የመጣ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ "በጋራ መክሮና ተቀናጅቶ መጓዝ ለውጤት እንደሚያበቃ ከአትሌቶቹ ድል መማር ይገባል" ብለዋል።

"አትሌቶቻችን በዓለም አደባባይ ከሜዳሊያ በተጨማሪ በሰላም አምባሳደርነት የኢትዮጵያን ታሪክ በደማቅ ቀለም መጻፋቸው የሁላችን ኩራት ነው፤ እኛም በልማቱ ታሪክ በመስራት ድሉን እናጠናክር" ሲሉም አቶ መንግስቱ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ጠላቶቻችን ሴራ ችግር ውስጥ ሆና በዓለም ላይ በአሸናፊነት ደምቃ በመታየቷ መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የጋሞ አባት አቶ ተፈራ ኦይቻ ናቸው።

"ህብረትና አንድነታችንን ካጠናከርን ሁሌም አሸናፊዎች ነን" ያሉት አቶ ተፈራ፣ ለዚህም የአድዋን ድል ጀግኖች አብሮነት በዋቢነት ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ ከአንድነት ውጭ አማራጭ ስለሌለ ከአትሌቶች ድል መደጋገፍና ለሀገር ክብር በጋራ መቆምን መማር እንደሚገባ ገልጸዋል።

"የጋራ ጥቅሞቻችንን እንዲከበሩ መቻቻል፣ አንድነትን ማጽናትና የጋራ እሴቶቻችንን ማጎልበት ወሳኝ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

የጋሞ አባቱ እንዳሉት ቀደምት አባቶቻችን ልዩነትን የሚያጎሉ ችግሮች ሳይገጥማቸው ቀርቶ ሳይሆን የውስጥ ጉዳያቸውን በውይይት እየፈቱ መምጣታቸው ለድል አብቅቷቸዋል።

በእዚህ አብሮነታቸው የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት አስጠብቀው ለዛሬ ትውልድ እንዳሻገሩም ተናግረዋል።

"አሁንም እንደ ሀገር የሚስተዋሉ ችግሮችን በንግግር በመፍታት ለቀጣይ ትውልድ የለማች ሀገር ለማስረከብ የዛሬ ትውልድ ሀላፊነት አለበን" ብለዋል።

በቀጣይም በችግር ውስጥ ኢትዮጵያ አሸንፋ እንድትወጣ ለማድረግ የቅርቡ የአትሌቶቹ ኢትዮጵያን ከፍ ያደረጉበት መንገድ ጥሩ ምሳሌ መሆኑንም አቶ ተፈራ ገልጸዋል።

በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያ በ4 ወርቅ 4 ብርና በ2 ነሀስ በድምሩ 10 ሜዳሊያ በመሰብሰብ በዓለም 2ኛ በአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ ሆና ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም