አንድነታችንን ካጠናከርን ሀገራችንን ከፍ ልናደርጋት እንደምንችል የአትሌቲክሱ ውጤት ማሳያ ነው- ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
አንድነታችንን ካጠናከርን ሀገራችንን ከፍ ልናደርጋት እንደምንችል የአትሌቲክሱ ውጤት ማሳያ ነው- ነዋሪዎች
ሶዶ፤ሐምሌ 20/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንን ካጠናከርን የትኛውንም ችግር በመቋቋም ሀገራችንን በዓለም አደባባይ ከፍ ልናደርጋት እንደምንችል አትሌቶቻችን በኦሪገኑ አትሌቲክስ ያስመዘገቡት ውጤት ማሳያ ነው ሲሉ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ኢዜአ ኢትዮጵያ በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከአለም 2ኛ ደረጃ በመያዝ ውድድሩን በበላይነት ማጠናቀቋን በማስመልከት ከወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ቆይታ አድርጓል ።
ነዋሪዎችቹ በሰጡት አስተያየት "ኢትዮጵያዊያን እንደቀድሞ አባቶች አንድነታችንን ካጠናከርን የሚያጋጥሙንን ችግሮች በመቋቋምና በመሻገር ሀገራችንን በዓለም አደባባይ ከፍ ልናደርጋት እንደምንችል አትሌቶቻችን በኦሪገኑ የዓለም አትሌትክስ ሻምፒዮና ያስመዘገቡት ውጤት ማሳያ ነው" ብለዋል ።
በኢትዮጵያዊያን ጥንካሬ በዓለም ደረጃ የተገኘውን ውጤት በልማቱም ለመድገም መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
የወላይታ የሀገር ሽማግሌ አቶ አብርሃም ባቾሬ "በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ብንሆንም አንድነታችንን አጠናክረን ከተባበርን በዓለም አደባባይ ራሳችንን ከፍ ልናደርግ እንችላለን" ብለዋል።
ጀግኖች አትሌቶቻችን ዓለምን ያስደነቀ ድል ማስመዝገብ የቻሉበት የስነ ልቦና ፅናት ከአንድነትና ከመተባበር መንፈስ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በውድድሩ የተገኘውን የአንድነት ውጤት በልማቱም ለመድገም መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት ሊጥሏት የሚፈልጉ ጠላቶች ያሏት ቢሆንም በልጆቿ የአልበገር ባይነት ፅናት ተከብራ መቆየቷን ገልጸዋል።
"ዘላቂ ሰላም በመገንባትና በአንድነታችን ሀገራችንን ቀና እናደርጋታለን" ሲሉ አቶ አብርሃም በአጽእኖት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያዊያን ስንተባበር ከኛ አልፎ ሀገራችን በዓለም ህዝቦች ፊት ከፍ እንደምትል ከሰሞኑ በአትሌቶቻችን የተገኘው ድል ማረጋገጫ ነው" ያሉት ደግሞ አቶ ሰይፉ ለታ ናቸው።
ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በውድድሩ ያሳዩትን አንድነት፣ ትብብርና የሀገር ፍቅር ጽናት ያደነቁት አቶ ሰይፉ "ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ለሀገር ያለንን ፍቅር የምናሳይበት ከመሆኑም በላይ ጠላቶቻችንን በማሳፈር ከመበታተን ይታደገናል" ብለዋል።
በኢትዮጵያዊያን ጀግኖች በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተመዘገበው ታላቅ ድል ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚሉ ህልመኞችን ተስፋ ያስቆረጠ መሆኑን ተናግረዋል።
"ከተባበርን የሀገራችን የብልፅግና ጉዞ እውን መሆኑ አያጠራጥርም" ያሉት አቶ ሰይፉ አለመግባባቶችን በሰላም በመፍታት አንድነታችንን እናጠናክር" ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
ወይዘሮ ዘነበች ደስታ የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው በውድድሩ የሚመዘገቡ ድሎች ነዋሪው ከሩጫና የስፖርት መንፈስ ባለፈ የአንድነትና ሀገራዊ ስሜቱን ሲገልጽ እንደነበር ተናግረዋል።
በነዋሪው ዘንድ “እኛ አሸነፍን” “ኢትዮጵያ አሸነፈች” በሚል ኢትዮጵያነት የተንጸባረቀበት ስሜት ሲገለጽ እንደነበር አስታውሰው "ኢትዮጵያዊያን ከቀደምት ታሪካችን ጀምሮ የሚያምርብን አንድነታችን ብቻ ነው" ብለዋል።
"አሁን ላይ ሀገር አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብትሆንም እንደ አትሌቲክሱ አይነት የጋራ ደስታ የሚፈጥሩ ድሎች ለአንድነታችን አስተዋፅኦ አላቸው" ሲሉም አክለዋል።
"እኛ ስንስቅ ሀገራችን ትስቃለች" ያሉት ወይዘሮ ዘነበች በአንድነታችንና በፍቅራችን የኢትዮጵያ አሸናፊነትን እናብስር" ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።