ቀጥታ፡

ለአትሌቲክስ ቡድኑ አቀባበል የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ይሆናሉ - የጋራ ግብረ ኃይሉ

ሐምሌ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ)በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተሳትፎ ውድድሩን በላቀ ውጤት ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ ሲገባ ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል።

በአቀባበሉ ወቅት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳያጋጥም የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ስለሚደረጉ ህብረተሰቡ የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ ተላልፏል።

በዚህ ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ተካፍለው አስደሳች ውጤት ላስመዘገቡት የአትሌቲክስ ቡድን አባላት ሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ/ም በአዲስ አበባ ደማቅ አቀባበል ይደረጋል።

የአትሌቲክስ ቡድኑ ከሚያርፉበት ስካይላይት ሆቴል ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ በአጀብ በአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች ስለሚጓዝ የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ይደረጋሉ።

የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብር ኃይል በተገኘው ውጤት የተሰማውን ደስታ እየገለፀ ቡድኑ ከስካይ ላይት ሆቴል ተነስቶ በቦሌ ጎዳና ፣ መስቀል አደባባይ ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ-ክርስቲያን ፣ ሂልተን ሆቴል ፣ ፓርላማ ፣ አራት ኪሎ ፣ ራስ መኮንን ድልድይ ፣ ፒያሳ ፣ ቸርችል ጎዳና ፣ ቴዎድሮስ አደባባይ፣ ብሔራዊ ቴአትር ፣ ሜክሲኮ አደባባይ ፣ ለገሃር ፣ መስቀል አደባባይ በማድረግ መዳረሻውን ብሔራዊ ቤተ-መንግስት ያደርጋል።

ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ከጠዋቱ 12፡00 ጀምሮ ለአጭርም ሆነ ለረጅም ሰዓት ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ የተከለከለ ሲሆን የአትሌትክስ ቡድኑ በአጀብ በሚያልፍበት ወቅት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳያጋጥም ከተፈቀደላቸው ተሽከርካሪዎች በስተቀር የተጠቀሱት መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ስለሚሆኑ ህዝቡ ይህን ተገንዝቦ የተለመደውን ትብብሩን እንዲያደርግ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ጥሪውን እያስተላለፈ ወደ ቦሌ አየር መንገድ የሚመጡ መንገደኞችና ሌሎች ተጠቃሚዎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

ህብረተሰቡ ለፀጥታው ስራ ስኬታማነት እያደረገ ላለው ቀና ትብብር ግብረሃይሉ ምስጋናውን እያቀረበ ትብብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

ከፀጥታ ጋር ተያያዥ መረጃ ወይም ጥቆማ ለመስጠት በ991 ወይም 816 ነፃ የስልክ መስመሮችን እና 01- 11 -11- 01 -11፣ 01- 11- 26- 43- 59፣ 01- 11- 01- 02- 97፣ መጠቀም እንደሚቻል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ አስታውቋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም